ዩናይትድ ስቴትስ ለሱዳኑ ጦርነት እልባት ፍለጋ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሾመች

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በካርቱም አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ

በሱዳን በአስር ሺዎች የተገደሉበትን እና ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን ጦርነት ለማቆም ዩናይትድ ስቴትስ በካርቱም አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሾማለች።

የሱዳኑ ግጭት ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ የቀድሞው ዲፕሎማት እና የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል ቶም ፔሪዬሎ የልዩ መልዕክተኝነት ሥራቸውን እንደሚጀምሩ የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ብሊንከን በመግለጫቸው አክለውም ‘ጦርነቱ እንዲያበቃ፣ ሰብአዊ ቀውሱ እና የጭካኔ አድራጎቶች እልባት ያገኙ ዘንድ ፔሪዬሎ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አጋሮቻቸውን በማስተባበር ጥረታቸውን ያጠናክራሉ’ ብለዋል።

ፔሪዬሎ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "ይህ ሹመት ፕሬዝዳንት ባይደን እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንከን ጦርነቱን እና ከግጭቱ ተዛምዶ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ ግፍ በማስቆም፤ እንዲሁም አስከፊው የሰብአዊ ቀውስ ወደ ለየለት ቸነፈር እንዳይሸጋገር ለመከላከል ለሁኔታው የሰጡትን ግምት እና አስቸኳይ ትኩረት ያሳያል" ብለዋል።

በሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የነበሩት ጆን ጋድፍሪ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ብሊንከን በመግለጫቸው አስታውሰዋል። አያይዘውም ዳንኤል ሩቢንስታይን የሱዳን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ሆነው በጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚነት እንደሚገለግሉ እና የጽ/ቤታቸው መቀመጫ በኢትዮጵያ እንደሚሆን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኝ የጦር አዛዦች መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዋን መዝጋቷና ጦር ሰራዊቷ በሀገሪቱ የነበሩትን የአሜሪካ መንግስት ሰራተኞች ከካርቱም ማውጣቱ ይታወሳል።