በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ግጭት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ማፈናቀሉን ተመድ አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ ከሱዳን ተሰደው ቻድ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች
ፎቶ ፋይል፦ ከሱዳን ተሰደው ቻድ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች

- በዳርፉር የከፋው ጥቃት “በሰብእና ላይ የተፈጸመ ወንጀል”ን ወደ ማቋቋም እያመራ ነው፤ ተብሏል

በሱዳን እየተካሔደ ያለው ግጭት፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ማፈናቀሉን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ትናንት ረቡዕ አስታውቋል። በዳርፉር እየተባባሰ የመጣው ጥቃት፣ “በሰብእና ላይ የተፈጸመ ወንጀል”ን ለማቋቋም ወደሚችልበት ደረጃ እያመራ እንደኾነ፣ አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን አስታውቀዋል።

ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ፣ በጦር ኃይሉ እና በተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል፣ በዋና ከተማዪቱ ካርቱም እና አካባቢዋ በተቀሰቀሰ ውጊያ፣ ሱዳን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ከባዱ ውጊያ ሲካሔድባቸው በሰነበቱት በዋና ከተማዋ ክፍሎች እና በዳርፉር፣ ትላንትም ውጊያው ቀጥሏል።

እስካለፈው ሰኞ ድረስ፣ በጦርነቱ ቢያንስ 959 ሰዎች ሲሞቱ፣ 4ሺሕ750 የሚደርሱ ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸውን፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚከታተለው የሱዳን ዶክተሮች ማኅበር አስታውቋል።

በምዕራብ ዳርፉር ዋና ከተማ ጄኒና እየተካሔደ ባለው ግጭት፣ የሟቾቹ ቁጥር ከዚኽም በላይ ሊኾን እንደሚችል፣ የዶክተሮቹ ማኅበር አመልክቷል።

በአሠቃቂው ግጭት ሳቢያ፣ ከ1ነጥብ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ መኖሪያቸውን በመልቀቅ ደኅንነታቸው ወደሚጠበቅበት ሌሎች የሱዳን አካባቢዎች መሰደዳቸውን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) አመልክቷል።

ሌሎች ወደ 530ሺሕ የሚደርሱ ሱዳናውያን ደግሞ፣ ወደ ግብጽ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሊቢያ መሰደዳቸውን፣ የፍልሰተኞቹ ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።

በ18ቱም የሱዳን ክፍለ ግዛቶች ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ፣ ከጠቅላላው የተፈናቃዮች ቁጥር 65 ከመቶ ያህሉን ካርቱም ይዛለች፤ ምዕራብ ዳርፉር 17 ከመቶ ተፈናቃዮችን በማስመዝገብ እንደምትለጥቅ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት (IOM) ድርጅት አስታውቋል።

እንደገና ወደ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያ እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተለውጦ፣ ወደ አስከፊ ወንጀል ሊያድግ እንደሚችል”

የምዕራብ ዳርፉር ግዛት አስተዳዳሪ ካሚስ አብደላ አብካር፣ የፈጥኖ ደራሹ ጦር እና አጋር ሚሊሻዎች፣ በጄኒና ዙሪያ ማኅበረሰቦችን ያጠቃሉ፤ ሲሉ ከሠዋል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባም ጠይቀዋል።

በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቮልከር ፔርቴዝ፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በሰጡት ቃል፣ የጄኒናው ጦርነት፥ “የጎሣ መልክ መያዙን” ተናግረዋል።

በአረብ ሚሊሻዎች እና የፈጥኖ ደራሹን ጦር መለዮ ልብስ በለበሱ ታጣቂዎች፣ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በስፋት እየታየ ነው፤” ያሉት መልዕክተኛው፣ እንዲህ ያለው ጥቃት ከተረጋገጠ፣ “በሰብእና ላይ ወደተፈጸመ ወንጀል ሊያድግ ይችላል፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሪሙ ደሪቱ፣ ከትላንት በስተያ ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ፣ “የሚሠቀጥጥ ጥቃት” ያሉትን የጂኒና ጥቃት አውግዘዋል።

እንዲህ ያለው ውጊያ፣ “እንደገና ወደ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያ እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተለውጦ፣ ወደ አስከፊ ወንጀል ሊያድግ እንደሚችል” አማካሪዋ አስጠንቅቀዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG