በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስለ እኛ

ስለእኛ

የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኤርትራ የራዲዮ ሥርጭቶችን ያስተላልፋል፡፡ የአማርኛ ፕሮግራም የሚሠራጨው ከአንድ መቶ ሚሊየን በላይ የሚሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብና እንዲሁም በመላ ዓለም ለሚገኙ ምንጮቻቸው ሁለቱ ሃገሮች ለሆኑ ማኅበረሰቦች ነው፡፡ አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም የታለመው ኦሮሚያ ውስጥ ለሚኖሩ ከአጠቃላዩ የሕዝብ ቁጥር 37 ከመቶ የሚሆነውን ለሚሸፍኑ ኢትዮጵያዊያን ሲሆን ትግርኛ ፕሮግራም ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ይደመጣል፡፡

የቪኦኤ አድማጮች ፕሮግራሞቻችንን በራዲዮ አጭርና መካከለኛ የአየር ሞገዶችና በሳተላይት እንዲሁም በዲጂታል መልክ የተሰናዱ መድብሎችን በእጅዎ ስልክና በማንኛውም ሞባይል መሣሪያ፣ እንዲሁም በማንኛውም ኮምፕዩተር ላይ ከኢንተርኔታ ያገኟቸዋል፡፡

በቪኦኤ የሚሠራጩ ዝግጅቶች የሚያተኩሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ ባሉ ክንዋኔዎች፣ በአካባቢያዊ፣ በአህጉራዊ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎችም ዓለምአቀፍ ዜናዎች ሲሆን በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በአሜሪካ ባሕሎች፣ ፖለቲካ፣ ወጎችና ልማዶች፣ መዋዕለ-ዜና፣ በምጣኔ ኃብት፣ በጤና፣ በትምህርት እና ሌሎችም ስፋት ያላቸው ጉዳዮች ላይ የሚሠናዱ ናቸው፡፡ የመዝናኛ ቅንብሮችም እየተዘጋጁ ይተላለፋሉ፡፡

ጋለፕ የሚባለው ዓለምአቀፍ ቅኝቶችን የሚያካሂድ ተቋም በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም ያካሄደው ጥናት ውጤት እንዳሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ በየሣምንቱ በሦስት ሚሊየን አዋቂዎች የሚደመጥ ግንባር ቀደም ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ከእነዚህ አድማጮች ውስጥ አርባ ከመቶ የሚሆኑት ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 24 የሆነ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚሁ የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ከዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) አድማጭ ጣቢያው የሚያስተላልፋቸው መረጃዎች “የማይጠራጠሩት፤ የሚያምኑት፤” መሆኑን አሳይቷል፡፡ የወቅቱን ክንዋኔዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ ያስቻላቸው መሆኑንም እነዚሁ ጥናቱ ያካተታቸው አድማጮቹ ተናግረዋል፡፡

ስለእኛ

ቪኦኤ (የአሜሪካ ድምፅ) ለነፃ መገናኛ ብዙኃን ያላቸው ቅርበት የተወሰነ ለሆነ ወይም ጨርሶውኑም ነፃ ፕሬስ በሌለባቸው ሃገሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሕዝቦች በአርባ አምስት ቋንቋዎች የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ዘገባዎች የሚያቀርብ በዓለም እጅግ ግዙፉ ባለብዙ ሚድያ የዜና አውታር ነው። በ1934 ዓ.ም.* የተቋቋመው የአሜሪካ ድምፅ ሁሉን አቀፍና ገለልተኛ ሽፋን የሚሰጥ ለአድማጭና ለተመልካችም ዕውነትን የሚናገር መገናኛ ብዙኃን ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ አካል የሆነው ቪኦኤ ሙሉ በጀቱ የሚሸፈነው በአሜሪካዊያን ግብር ከፋዮች ነው።

የአሜሪካ ድምፅ ተልዕኮና ኤዲቶሪያል ነፃነት የቪኦኤን ጋዜጠኞች ከተፅዕኖ፣ ከጫና ወይም በመንግሥት ባለሥልጣናትና በፖለቲከኞች ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት ወይም የበቀል አድራጎት በሚጠብቋቸው ሕግጋት የተረጋገጠ ነው።

ሐምሌ 5/1968* ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ጀራልድ ሩዶልፍ ፎርድ የፈረሙት የቪኦኤ ቻርተር የሚከተሉትን ደንግጓል፤

1. ቪኦኤ ያለማቋረጥ ተዓማኒና አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። የቪኦኤ ዜና ትክክለኛ፣ ገለልተኛና ሁሉን አቀፍ ይሆናል።

2. ቪኦኤ የሚያሳየው ማንኛውንም አንድ ነጠላ አሜሪካዊ ኅብረተሰብ ሳይሆን አሜሪካን ነው፤ ስለሆነም የጎላ አሜሪካዊ አስተሳሰብንና ተቋማትን ሚዛናዊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ያቀርባል።

3. ቪኦኤ የዩናይትድ ስቴትስን ፖሊሲዎች በግልፅና በውጤታማ ሁኔታ ያሳውቃል፤ በፖሊሲዎቹ ላይ የሚነሱ ኃላፊነት የተሞላቸው ውይይቶችንና አስተያየቶችን ያቀርባል።

በ1986 ዓ.ም.* የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ብሮድካስቲንግ ሕግን አፀደቀ። ይህ ህግ የቪኦኤ ጋዜጠኞች የሚታመኑ፣ ትክክለኛ፣ ገለልተኛ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ሚዛናዊና የዩናይትድ ስቴትስን ባሕላዊና ማኅበራዊ ስብጥር የሚያሳዩ እንዲሆኑ ያዝዛል።

የተወካዮች ምክር ቤቱ በ2008 ዓ.ም.* ባወጣው የብሔራዊ መከላከያ አፈፃፀም ማረጋገጫ ሕግ ላይ ዜናን የማሰባሰብና የመዘገብ ሥራዎች ነፃና ገለልተኛ በመሆናቸው መቀጠል እንዳለባቸው እንደገና አረጋግጧል።

የቪኦኤ ጋዜጠኞች ለዓለም የነፃ ፕሬስ መርኆች ተምሣሌት ይሆኑ ዘንድ በየዕለቱ ጠንክረው ይሠራሉ።

ቪኦኤ

ነፃ መገናኛ ብዙኃን ብርቱ ፋይዳ አላቸው

* የዘመን አቆጣጠር - ሁሉም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው።

XS
SM
MD
LG