የሱዳን ህዝብ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ መሆኑን እና ዓለም ድጋፍ ካላደረገላቸው፣ ሁኔታው እየከፋ ሄዶ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን አስታወቁ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከስድስት ወራት በፊት ሁለቱ ተቀናቃኝ ጀነራሎች ወደጦርነት ከገቡ ወዲህ፣ ሱዳን ከዓለም በከፍተኛ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ የመፈናቀል ቀውስ ያለባት ሀገር ሆናለች። እስካሁን 5.4 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በሱዳን ውስጥ ተፈናቅለዋል ወይም ወደ ጎረቤት ሀገሮች ተሰደዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ክሌመንቲን ንክዌታ ሳላሚ እንደሚሉት "በቀን በአማካይ ከ30ሺህ በላይ ሰዎች ልብሳቸውን ብቻ ይዘው ይሰደዳሉ።"
ሳላሚ በጄኔቫ ለአንድ ሳምንት ባደረጉት ቆይታ ከእርዳታ ሰጪ ሀገራት ጋር ተገናኝተው በጣም ዝቅተኛ የገንዘብ ድጋር እየተደረገለት ላለው የሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ እርዳታ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በሱዳን የነፍስ አድን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ከ18 ሚሊየን በላይ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ ከተጠየቀው 2.6 ቢሊየን ዶላር ውስጥ እስካሁን የተገኘው አንድ ሶስተኛው ብቻ ነው።
ሳላሚ እንደሚሉት በሱዳን የሚገኙት 70 ከመቶ ሆስፒታሎች አገልግሎት የማይሰጡ በመሆናቸው፣ ሱዳናውያን የጤና አገልግሎት ማግኘት አይችሉም። በተለይ በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ተጨማሪ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል በተሰጋበት እና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ በታወጀበት ወቅት፣ የጤና አገልግሎት አለመኖሩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት ባለስልጣኗ አብራርተዋል።
መድረክ / ፎረም