በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተባባሰው የሱዳን ግጭት በጎረቤት ሀገራት ላይ አደጋ ጋርጧል


የተባባሰው የሱዳን ግጭት በጎረቤት ሀገራት ላይ አደጋ ጋርጧል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:29 0:00

የተባባሰው የሱዳን ግጭት በጎረቤት ሀገራት ላይ አደጋ ጋርጧል

ምንም መሻሻል ያላሳየው፣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ንግግር እና የቀጠለው ግጭት፣ በጎረቤት ሀገራትም ላይ አደጋ መጋረጡን ተንታኞች አስጠነቀቁ፡፡ “አንድ ቀን ሱዳን፣ ከወታደራዊ ይልቅ በሲቪሎች የሚመራ መንግሥት ሊኖራት ይችላል፤” በሚለው የሱዳናውያን ተስፋ ላይ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ተንታኞች ጠቁመዋል።

በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከ25 ቀናት በኋላም ውጊያው እንደቀጠለ ሲኾን፣ ተፋላሚዎቹ ጎራዎች ግጭቱን ለማቆም የመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው የሚጠቁም ምንም ዓይነት ፍንጭ አይታይም።

በቅርቡ፣ በናይሮቢ ጉብኝት ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ አቪና ሻምዳሳኒ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ የአየር ጥቃቶቹ አሁንም እንደቀጠሉ መኾናቸውን ገልጸው፣ እጅግ አሳሳቢ እንደኾነ አመልክተዋል። “ፈጥኖ ደራሹ ኃይል፣ የፕሬዚዳንቱን ሕንፃዎች ሳይቀር ለወታደራዊ ዒላማ መቆጣጠሩን እንደቀጠለ ነው፤” ያሉት ሻምዳሳኒ፣ “ለመሸሽ የሚሞክሩ ሰዎችም፣ በመንገድ ላይ የጸጥታ ስጋት ብቻ ሳይኾን ዘረፋም ይደርስባቸዋል። ከፍተኛ የመድኃኒት፣ የምግብ እና የነዳጅ እጥረት አለ። ኹኔታው እየተባባሰና ወደ ከፍተኛ ግጭት እያመራ ነው፤” ሲሉ አሳሳቢነቱን ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ፥ አካባቢውን የሚያካልል ቀጣናዊ እና ከዚያም ያለፈ ጉዳት የማድረስ ዐቅም አለው፤ በማለት ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ፣ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲካን የሚያስተምሩት ኩዋኩ ንዋማህ ናቸው። ሱዳን ሰባት ጎረቤቶች እንዳሏት ያመለከቱት ንዋማህ፣ ሁሉም በተወሰነ ደረጃ አለመረጋጋት ያለባቸው በመኾኑ፣ ግጭቱ በደቂቃ ውስጥ ቀጣናዊ ሊኾን ይችላል፤ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ወደ ሳዑዲ አረብያ እና የመንም ሊዛመት ይችላል፤ ብለዋል።

የሱዳን ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ተወካዮች፣ በሳዑዲ አረቢያ የወደብ ከተማ በኾነችው ጅዳ ሲገናኙ ቆይተዋል። የዚኽ ውይይት ዋና ዓላማ፣ ግጭት ለማቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስና ሰፊ ለኾኑ ውይይቶች መሠረት መጣል ቢኾንም፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ተቋም የአፍሪካ ዲሬክተር ሱዛን ስቲጋንት፥ ብዙ ሰዎች፣ ማንኛውም የወደፊት ፖለቲካ ውይይቶች ማዕከል ሊኾኑ የሚገባቸውና በሱዳን ውስጥ ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ግንባር ቀደም ተሰላፊ በኾኑ ሲቪል ዜጎች እና የፖለቲካ አመራሮች ሚና ላይ፣ ጥያቄዎችንና ስጋቶችን እየገለጹ መኾኑን በማመልከት፣ ሱዳን በሲቪል ወደሚመራ መንግሥት የመመለሷ ጉዳይ ስጋት ላይ መውደቁን ያስረዳሉ።

የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል መሪ የኾኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ፣ በቅርቡ በትዊተር ገጻቸው ላይ በአስተላለፉት መልዕክት፣ እርሳቸውም ኾኑ ኃይላቸው፣ “በዴሞክራሲ እና በሲቪል ለሚመራ መንግሥት ሽግግር” ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ተቀናቃኛቸው የኾኑትና የሱዳንን ጦር የሚመሩት ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን ግን፣ እንዲህ ዐይነት ቃል አልገቡም። ኾኖም፣ ዳጋሎ እና ቡርሃን፣ እ.አ.አ በ2021 በሲቪል እና ወታደራዊ ጥምረት ይመራ የነበረውን መንግሥት ለመጣል ተባብረዋል።

በሱዳን እየተካሔደ ያለው ግጭት፣ ብዙዎችን ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ ሲያደርግ፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ቻርሎቴ ኾልኩዩስት እንደሚሉት፣ በርካታ ሱዳናውያን፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት በተካሔደ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ጥለው ወደሸሿት ደቡብ ሱዳንም ተሰድደዋል።

ስለዚኽም ሲያብራሩ፣ “እስከ አሁን፣ ወደ 45ሺሕ የሚጠጉ ሰዎችን መዝግበናል፤ ነገር ግን ቁጥሩ ከዚያም በላይ ሊኾን ይችላል። ለሁለተኛ ጊዜ መፈናቀል አሳዛኝ ነገር ነው። በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት፣ በሱዳን የተሻለ ደኅንነት ለማግኘት ነበር የተሰደዱት። አሁን ደግሞ መልሰው ወደ ደቡብ ሱዳን እየተሰደዱ ነው፤” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባይዋ አክለውም፣ ብዙዎች፥ በላይኛው ዓባይ ወደሚገኘው ደቡብ ሱዳን ለመሻገር በእግር፣ በአውቶቡስ ወይም በአህያ የሚጎተት ጋሪ በመጠቀም፣ ረጅም ቀናትን በመንገድ ላይ ማሳለፋቸውን ይገልጻሉ። እጅግ ደክመውና ተርበው እንደሚደርሱ በመጥቀስም፣ የስደተኛ መርጃ ተቋሙ፣ በድንበር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ እየሰጠና ሰዎቹን ሬንክ ወደተባለች ከተማ እያጓጓዘ መኾኑን አስረድተዋል።

ኾኖም ይላሉ ኾልኩዩስት፣ “ሬንክ ያለው ዐቅም ውስን በመኾኑ፣ ሰዎቹ ከዚያም እንዲነሡ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ያበረታታል።”

የአሜሪካ ድምፅዋ ማሪያማ ዲያሎ፣ ከናይሮቢ ያደረሰችን ዘገባ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

XS
SM
MD
LG