በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የጎሳ ግጭት ካለፈው ሐምሌ ወዲህ 359 ሰዎች ተገደሉ


የሱዳን ካርታ
የሱዳን ካርታ

ግጭት ባልተለየው የሱዳን ደቡባዊ ክፍል ላለፉት አራት ወራት ሲካሄድ በሰነበተው የጎሳ ግጭት እስከ 359 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተመድ ዓለም አቀፍ የስደኞች ድርጅት (አይኦኤም) ትናንት አስታወቀ። ይህም ቀውስ ውስጥ ባለችው ሱዳን ጠረፋማ አካባቢዎች ሁከት በከፍተኛ ደረጃ እየጋመ መምጣቱን አመላካች ነው ተብሏል።

ብሉ ናይል ስቴት በተባለው ግዛት ባለፈው ሐምሌ የጀመረው ሁከት 97 ሺህ ሰዎች እንዲፈናቀሉና 469 ስዎች እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል ሲል የስደተኞች ወኪሉ አስታውቋል።

ከሁለት ሣምንት በፊት መነሻቸው ምዕራብ አፍሪካ በሆነው በሃውሳ ጎሳ እንዲሁም በበርታና ሃማጅ ጎሳዎች መካከል በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በተከሰተው ግጭት በ48 ሰዓት ውስጥ ብቻ 230 ሰዎች ተገድለዋል።

ሁከቱ እየተካሄደ ያለው ሃግሪቱን እየገዙ ያሉ ጄኔራሎች እና የዲሞክራሲ አቀንቃኞች በዓለም አቀፍ ወገኖች በመታገዝ የሃገሪቱ ፖለቲካ ሁኔታ ለማሻሻል ውይይት ላይ ባሉበት ወቅት ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት የሱዳን ወታደራዊ መሪ የሆኑት ጄኔራል አብደል-ፈታህ ቡርሃን በሲቭልና ወታደሮች የተዋቀረውን የሽግግር አስተዳደር በመፈንቅለ-መንግስት አስወግደው ስልጣኑን ከጨበጡ ወዲህ ሃገሪቱ ምስቅልቅል ውስጥ ገብታለች።

ለ26 ዓመታት ሲገዙ የነበሩት ኦማር አል-ባሺር በሕዝባዊ አመጽ ሲወገዱ፣ በሲቭልና ወታደሮች የተዋቀረው አስተዳደር ሱዳንን ወደ ዲሞክራሲ ያሸጋግራል የሚል ተስፋ ጭሮ ነበር።

የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ እየተባለ የሚተራው አካል ባወጣው አሓዝ መሰረት ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በተካሄደ ተቃውሞ ወታደራዊ አገዛዙ 118 ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ገድሏል።

በሃገሪቱ ጠረፍ አካባቢዎች እየጋመ የመጣው የጎሳ ግጭት፣ ወታደራዊው አስተዳደር በካርቱምና በሃገሪቱ ማዕከላዊ አካባቢዎች የተነሳበትን ተቃውሞ በመጨፍለቅ ሥራ ላይ በመጠመዱ በተፈጠረ ክፍተት ምክንያት ነው ሲሉ ብዛት ያላቸው ተንታኞች ይገልጻሉ ሲል የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG