ዋሽንግተን ዲሲ —
በሱዳን ወታደራዊ አገዛዙን በመቃወም የሚካሄደው ሰልፍ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ትናንት እሁድ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞ የተሳተፉበትን ሰልፍ ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች የአስለቃሽ ጋዝና ተቀጣጣይ መሣሪያዎችን መጠቀማቸው ተገለጸ፡፡
የሱዳን የህክምና ባለሙያዎች አንድ ተቃዋሚ መገደሉን የገለጹ ሲሆን ይህም እስከዛሬ በተቃውሞ የተገደሉትን ሰዎች 62 እንደሚያደርሰው ተመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት ወታደራዊ መሪዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎች ቡድኖች እንዲነጋገሩ ሙክራ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በመፈንቅለ መንግሥቱ ተወግደው እንደገና ወደ ሥልጣን ተመልሰው የነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ፣ በወታደራዊው ክፍልና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ቅራኔ መፍታት ባለመቻላቸው ታህሳስ 24/ 2014 ዓ.ም ከሥልጣን የለቀቁ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡