በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ልዑክ ከሱዳን መሪዎች ጋር ተገናኙ


የዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጀፍሪ ፊልትማን
የዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጀፍሪ ፊልትማን

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ዴሞክራሲን ለማስፈንና ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚደረገውን ሽግግር እንደምትደግፍ የዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጀፍሪ ፊልትማን አስታወቁ፡፡

ፊልትማን ይህን ያስታወቁት፣ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብድላ ሀምዶክ እና፣ ከልዕልና ምክር ቤት መሪ ጀኔራል አብዱል ፈታ አልቡርሃን፣ እንዲሁም ከምክትላቸው ጀኔራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጋር ትላንት ቅዳሜና ዛሬ እሁድ በካርቱም ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው፡፡

ፊልት ማን በትዊት መልክታቸው፣ ሁሉም ወገኖች የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ኦሞር አልበሽር መንግሥት መወገድ ምክንያት ከሆነው ከእኤአ ከ2018 እስከ 2019 የተቃውሞ እንስቃሴ በኋላ የደረሱበትን ህገመንግሥታዊ ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በሱዳን ሥልጣን በተጋሩት የሲቪልና ወታደራዊ አስተዳደሮች መካከል መስከረም ወር ውስጥ ተደርጓል ከተባለው የመንፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወዲህ ከፍተኛ መቃቃር ተፈጥሯል፡፡

የኢኮኖሚው ቀውስ እየበረታ በመምጣቱ፣ የቅንጅቱ አባል የነበሩት አማጽያን ቡድኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወታደሩ ጋር በመወገን፣ "የሲቪል አስተዳደር ሥልጣን እየጠቀለለና የአስተዳደር ብልሹነት እያሳየ ነው" በሚል ካቢኔው እንዲበተን ይፈልጋሉ፡፡

ይህንን በመቃወም ፣ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ የሱዳን ዜጎች፣ ባለፈው ሀመሱ በካርቱምና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ በርካታ የካቢኔ ሚኒስትሮችም የተቃውሞው ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የሱዳን ወታደራዊ መሪ፣ ጀኔራል አልቡርሃን ከፊልት ማን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ባወጡት መግለጫ፣ ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ዩናይትድ ስቴትስ የምታደርገውን ድጋፍ አድንቀው፣ ሠራዊቱም ያንን ሽግግር ለመጠበቅ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG