በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ


የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:40 0:00

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

አራት ቀናት ባስቆጠረው ውጊያ ቢያንስ 185 ሰዎች ተገድለዋል

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንሥቶ ሲፋለሙ የቆዩት፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ድጋፍ ሰጪ ኃይል፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ የ24 ሰዓት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን፣ የአረብ ብዙኃን መገናኛዎችን ጠቅሶ አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የሳተላይት የዜና ማሠራጫ አውታር የኾኑት አል-አረቢያ እና አልጃዚራ፣ ከፍተኛ የጦር መኰንን የኾኑትን ሻምስ ኤል ዲን ካባሽን ጠቅሰው፣ ተፋላሚ ወታደራዊ ኃይሎቹ፥ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና ስምምነቱንም እንደሚያከብሩ መናገራቸውን አመልክተዋል።

ቀደም ሲልም፣ የሲኤንኤን የአረብኛ ቋንቋ ክፍል፥ የአገሪቱን የጦር አዛዥ አብደል ፈታሕ አል ቡርሃንን ጠቅሶ በአወጣው ዘገባ፣ ኃይላቸው፣ ለአንድ ቀን በሚቆየው የተኩስ ማቆም ስምምነት እንደሚሳተፍ አስታውቋል።

የ24 ሰዓት የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ የተደረሰው፣ በሱዳን የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ተሽከርካሪዎች የተኩስ ጥቃት ከደረሰባቸውና ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች፣ ከባድ መሣሪያዎችን በመጠቀም ለአራት ተከታታይ ቀናት ከተዋጉ በኋላ ነው።

በሱዳን የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን የሚመራውና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ወይም በምሕጻረ ቃሉ - አርኤስኤፍ ተብሎ የሚጠራው ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው ቡድን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት፣ በትንሹ 185 ሰዎች የተገደሉ ሲኾን፣ የአገሪቱ የጤና ሥርዐት መፈራረስን ጨምሮ አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ መቀስቀሱን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የሳተላይት ምስል፣ የሱዳን ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መውደሙን እና አውሮፕላኖች መውደማቸውን የሚያሳይ ምስል። (ማክስር ቴክኖሎጂዎች/ሮይተርስ )
የሳተላይት ምስል፣ የሱዳን ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መውደሙን እና አውሮፕላኖች መውደማቸውን የሚያሳይ ምስል። (ማክስር ቴክኖሎጂዎች/ሮይተርስ )

ተዋጊዎቹ፥ የርዳታ ሠራተኞችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት ተሽከርካሪንና የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር መኖሪያን ጨምሮ ሌሎች ዲፕሎማቶችን ማጥቃታቸው ሲገለጽ፤ ባለፈው ቅዳሜ፣ በዳርፉር በተካሔደ ውጊያ፣ ሦስት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞችን መግደላቸውንና የመንግሥታቱ ድርጅትን አውሮፕላን መምታታቸውም ተዘግቧል።

ከቀናት ውጊያ በኋላ፣ የመንግሥቱን የቴሌቭዥን ማሠራጫ ጣቢያ መቆጣጠሩን ያስታወቁት፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ፣ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋራ በስልክ በአደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኹኔታዎች በቁጥጥር ሥር መኾናቸውንና የሱዳን ጦር እንቃስቃሴውን ከዚኽ በላይ ማስፋት እንደማይሻ አመልክተዋል።

ቃል አቀባዩ፣ አሁን ኹኔታው በቁጥጥር ሥር እንደዋለና ድንጋጤውን የማጥፋትና ለሚቀጥሉት ደረጃዎች ኹኔታውን ለማመቻቸት የተደረገ የመጀመሪያ ርምጃ እንደነበር አስገንዝበዋል።በስኬት የተጠናቀቀ ደረጃ ነው። ብዙ የአርኤስኤፍ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ በርካቶች ለጦሩ እጃቸውን ሰጥተዋል፤” ብለዋል።

የጦር ኃይሉ፣ ከቀናት ውጊያ በኋላ አርኤስኤፍን በመመከት፣ በኦምዱርማን ከተማ የሚገኘውን ዋና የቴሌቪዥን ሕንፃ መቆጣጠሩን አስታውቋል። በመንግሥት የሚንቀሳቀሰው የሱዳን ቴሌቪዥንም፣ ተቋርጦ የነበረውን ሥርጭቱን ቀጥሏል።

ፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል፣ ባለፈው እሑድ በአወጣው መግለጫ፣ መደበኛው ጦር የአየር ጥቃት ያደረሰበትን ኦምደርማን የሚገኘውን የጦር ሰፈር ጥሎ መውጣቱን ተናግሯል። በኢንተርኔት አማካይነት የተለቀቁ የቪዲዮ ምስሎችም፣ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ናቸው፤ ያሏቸውን ደርዘን የሚያህሉ አስከሬኖች፥ በጦር ሰፈሩ አልጋ ላይ፣ በክሊኒኩ ወለል እና በግቢው ውስጥ ተበታትነው አሳይተዋል። የቪዲዮቹ ትክክለኛነት በገለልተኛ ቡድን አልተረጋገጠም።

የአገሪቱ መደበኛ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ፣ በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ክልል እና ከግብፅ እና ከኢትዮጵያ ጋራ በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች በሚገኙ የሰሜንና የምሥራቅ ክፍል አካባቢዎችን ጨምሮ በአገሪቱ ዋና ዋና ማዕከሎችም ውጊያ አካሒደዋል። ባለፈው ሰኞ፣ ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው መርዌ በተሰኘች ስትራቴጂያዊ የአየር ማረፊያ አቅራቢያም ውጊያ የተካሔደ ሲኾን፣ ኹለቱም ወገኞች ተቋሙን እንደተቆጣጠሩ በየራሳቸው አስታውቀዋል።

ሁለቱ ተፋላሚ የሱዳን ጦር ኃይሎች

የሥልጣን ሽኩቻው ያፋለማቸው ኹለቱ ኃይሎች፣ ቀደም ሲል አጋሮች የነበሩ ሲኾን፣ እ.አ.አ በጥቅምት 2021 የተካሔደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በጋራ አስተባብረዋል። ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደረገ ጫና፣ ቡርሃንና ዳጋሎ፣ በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና የዴሞክራሲ ደጋፊ ቡድኖች ጋራ በተወሰኑ ማኅቀፎች ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ የአርኤስኤፍ ታጣቂዎችን ከጦር ኃይሉ ጋራ በማዋሐድ እና ወደፊት በሚኖረው የሥልጣን ተዋረድ ረገድ ያለው ቅራኔ እያየለ በመምጣቱ፣ ስምምነቱን የመፈራረሙ ሒደት በተደጋጋሚ ተስተጓጉሏል።

በሱዳን የዳርፉር ግዛት ጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ጦራቸውን የገነቡት ዳጋሎ፣ ራሳቸውን የዴሞክራሲ ጠበቃ አድርገው ይመለከታሉ፤ ቡርሃንን ደግሞ “አጥቂ እና አክራሪ ሙስሊም” አድርገው ይፈርጇቸዋል። ኾኖም፣ ሁለቱም ጀነራሎች፣ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው፤ ኃይሎቻቸውም የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ላይ ርምጃ ወስደዋል።

ዳጋሎ፣ ባለፈው ማክሰኞ በአሰፈሩት ተከታታይ የቲዊተር መልዕክት፣ ከብሊንከን ጋራ ከተነጋጋሩ በኋላ፣ የ24 ሰዓቱን የተኩስ ማቆም ስምምነት መቀበላቸውን አስታውቀዋል። የጦር ኃይሉ መግለጫ በአንጻሩ፣ “ከአደራዳሪዎች ጋራ ስለተደረገ ምንምይነት ግንኙነት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስተባብሎ፣ ጦርነቱ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩንና በመጪዎቹ ሰዓታት የአርኤስኤፍ አስከፊ ሽንፈት እንደሚከሠት” ተናግሯል።

የጦር ሠራዊቱ ንብረት የኾኑ ተጨማሪ ታንኮች እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ ማክሰኞ ረፋድ ወደ ካርቱም ሲገቡ፣ ወደ ጦሩ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት እና የመንግሥቱ መቀመጫ ወደ ኾነው ቤተ መንግሥት ማምራቱን የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ሱዳናውያን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

ውጊያው ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ቢያንስ 185 ሰዎች መገደላቸውንና ከ1ሺሕ 800 በላይ መቁሰላቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ቮልከር ፔርቴስ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ሁለቱም ወገኖች፥ ታንኮችን፣ መድፎችንና ሌሎች ከባድ መሣሪያዎችን፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጭምር በመጠቀም ላይ እንዳሉ፣ ተዋጊ ጀቶች ዝቅ ብለው ሲበሩ እና ምሽት ላይ ከአየር መቃወሚያዎች የሚወጣው እሳት ሰማዩ ላይ ሲያበራ ታይተዋል።

በግጭቱ ምክንያት ለመድረስ አዳጋች በኾኑ የማዕከላዊ ካርቱም ጎዳናዎች፣ ብዙ አስከሬኖች ታይተዋል፡፡ ከዚኽ በመነሣት፣ የጉዳቱ መጠን ከዚኽም በላይ ሊኾን እንደሚችል ተገምቷል። እስከ አሁን ምን ያህል ሲቪሎች እና ተዋጊዎች እንደተገደሉ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣የሕክምና ባለሞያዎች ማኅበር፣ የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር 97 መድረሱን ገልጿል።

በሳምንቱ መጨረሻ፣ በ10 ሺሕዎች በሚቆጠሩ በከባዱ የታጠቁ ተዋጊዎች የተደገፉት ሁለቱ ተፋላሚ ጀነራሎች መሀከል የተፈጠረው ድንገተኛ ግጭት፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤታቸው ወይም ካሉበት መጠለያቸው እንዳይወጡ አግቷቸዋል፡፡ መሠረታዊ አቅርቦቶች እየተሟጠጡ በመኾኑ፣ በርካታ ሆስፒታሎች አገልግሎታቸውን ለማቆም ተገደዋል።

በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሻሂ ሻጮችንና ሌሎች የምግብ አምራጮችን ያቀፈው የሠራተኞች ማኅበር ሓላፊ አዋደያ ማሐሙድ፣ በደቡባዊ የካርቱም አውራጃ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “የጥይት ተኩስ እና የቦምብ ፍንዳታ በየቦታው ይሰማል፤” ብለዋል። ባለፈው እሑድ፣ የተወረወረ ቦምብ በጎረቤት ላይ ማረፉንና ቢያንስ ሦስት ሰዎችን መግደሉን የጠቀሱት ማሐሙድ፣ አስሬናቸውን፥ ወደ ሆስፒታል ለመውሰድም ኾነ ግብአተ መሬታቸውን ለመፈጸም አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በማዕከላዊ ካርቱም፣ የማያቋርጥ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ፣ የውጊያው ግንባር በኾነው የጦሩ ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ፣ ነጭ ጢስ እየተትጎለጎለ ሲወጣ ይታያል። በአቅራቢያው በሚገኘው የካርቱም ዩኒቨርሲቲ የምሕንድስና ኮሌጅ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ቀን አንሥቶ ቢያንስ 88 ተማሪዎች እና ሠራተኞች ተሸሽገው እንደሚገኙ፣ አንድ ተማሪ በኢንተርኔት በአስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት አስታውቋል። ከውጭ በነበረው ውጊያ፣ አንድ ተማሪ መሞቱንና ሌላ አንድ ተማሪ ደግሞ መቁሰሉንም ገልጿል። ምግብም ኾነ ውኃ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ የተኙ ሰዎችን አሳይቷል።

ለዐሥርት ዓመታት በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የኖሩት ሱዳናውያን፣ በሲቪል መንግሥት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመፍጠር እየጣሩ ባሉበት ወቅት የተፈጠረው ይኸው ግጭት፣ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል፤ የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።

ሱዳን፣ በርካታ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ታሪክ ያላት ሀገር ብትኾንም፣ በዋና ከተማዋ እና በዓባይ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ፣ እንደዚኽ ዐይነት ግጭት ታይቶ አይታወቅም። አለመረጋጋቱ የደፈረሰው፣ ሱዳናውያን የረመዳን ጾም መገባደጃ የኾነውን የኢድ አልፈጢርን በዓል ሊያከብሩ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነው።

በአሁኑ ወቅት በዋና ከተማው እና ሁለቱም ወገኖች በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን በየመንደሩ በአሠማሩባት በኦምዱርማን ከተማ በርካታ አካባቢዎች ከባድ የተኩስ ልውውጥ እየተካሔደ ነው። በመዲናዋ አቅራቢያ ያሉ 12 ሆስፒታሎች፣ ሠራተኞቻቸው በመፈናቀላቸው፣ እንዲሁም በጥቃት ወይም በመብራት መቆራረጥ ምክንያት አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ የሕክምና ማኅበሩ ገልጿል። ከ20 ሆስፒታሎች መሀከል፣ ከመዲናዪቱ ወጣ ብለው የሚገኙት አራት ሆስፒታሎች መዘጋታቸውን፣ ማኅበሩ፣ ሰኞ ምሽት በአወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ካርቱም ውጥ ሱቆች /ሚያዚያ 10/2015 ዓ.ም
ካርቱም ውጥ ሱቆች /ሚያዚያ 10/2015 ዓ.ም

ሀዲያ ሰዒድ በምትኖርበት፣ በሰሜን ካርቱም ባሃሪ አውራጃ አቅራቢያ፣ የሚሰማውን የተኩስ እሩምታ እና የቦምብ ፍንዳታ በመፍራት፣ ከሦስት ልጆቿ ጋራ ከመኖሪያ ቤቷ ወለል በታች ባለ አንድ ክፍል ውስጥ መደበቃቸውን ትገልጻለች። ለተጨማሪ ጥቂት ቀናት ምግብ አለን፤ የምትለው ሰዒድ፣ ከዚያ በኋላ ግን ምን ማድረግ እንደሚኖርብን አናውቅም፤” ትላለች።

በካርቱም ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው ጋብራ ሰፈር የሚኖሩ ነዋሪዎችም፣ ሰኞ ከሰዓት በኋላ፣ በከባድ መሣሪያዎች የታገዘ ውጊያ መቀጠሉን ይገልጻሉ። ከቤታቸው መውጣት ያልቻሉ ሰዎችም ይጮኹ እንደነበር በአካባቢው የሚኖሩ የሕክምና ባለሞያ አስማ አልቱም ተናግረዋል። በተለይ፣ በሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ ጣቢያዎች እና ቁልፍ የመንግሥት ሕንፃዎች አቅራቢያ፣ ኃይለኛ ውጊያ እየተካሔደ ሲኾን፣ ሁሉም ሥፍራዎች በመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በሱዳን ተደርጎ የነበረው ሕዝባዊ ዐመፅ፣ ዓምባገነን መሪ የነበሩትን ሐሰን ኦማር አል-በሽርን ከሥልጣን ከአስወገደ ወዲህ፣ አገሪቱ በተስፋ ተሞልታ ነበር። ኾኖም፣ እ.አ.አ ከ2021 መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በአገሪቱ የተንሰራፋው አለመረጋጋት፣ የዴሞክራሲ ተስፋውን አጨልሞ ኢኮኖሚውን አድቅቆታል። በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችው እና በሕዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ሦስተኛ ትልቋ ሀገር ሱዳን፣ 16 ሚሊየን(?) ከሚጠጋው ሕዝቧ አንድ ሦስተኛ የሚኾነው፣ ሰብአዊ ርዳታ ጠባቂ ኾኗል።

ዓለም አቀፍ ጫናው ተጠናቅሮ ቀጥሏል

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ አካላት፣ የእርቅ ጥሪ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ለሱዳር ጦር ድጋፍ የምትሰጠው ግብጽ እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የየመንን ጦርነት ለመደጋፍ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን በመላካቸው፣ ከፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል ጋራ የጠበቀ ግንኙነት የፈጠሩት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም እንዲሁ፣ ሁለቱም ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ ሰኞ ማምሻውን እንደተናገሩት፣ ካይሮ፣ ከሁለቱም የጦር ኃይሎች ጋራ ግንኙነት እያደረገች እንደኾነና ግጭቱን አቁመው ወደ ውይይት እንዲመለሱ እየወተወተች መኾኑን አስታውቀዋል። ይኹንና ሁለቱም ጀነራሎች፣ እስከ አሁን አንዱ ሌላውን እጅ እንዲሰጥ ከማሳሰብ አልፈው፣ ፍጹም ድምሰሳውን እንዲጠብቅ በመፎከር ላይ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ፥ ከአረብ ሊግ፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከአካባቢው መሪዎች ጋራ እየመከሩ መኾኑን ገልጸው፣ ሰላምን ለማስፈን ማንኛውም ተጽእኖ እና ግፊት እንዲደረግ አሳስበዋል።

ሁለቱንም ተቀናቃኝ ጀነራሎችን በተናጠል በስልክ ያነጋገሩት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ ባለፈው ሰኞ፣ በጃፓን በተካሔደው የቡድን ሰባት የበለጸጉ ሀገራት ስብሰባ ላይ በአደረጉት ንግግር፣ ሱዳናውያን፥ “ወታደሩ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ይሻሉ፤ ዴሞክራሲን ይናፍቃሉ፤ በሲቪል የሚመራ መንግሥትን ተስፋ ያደርጋሉ፤ ሱዳን ወደዚያ መንገድ መመለስ አለባት፤” ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሓላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው፣ የኅብረቱ የሱዳን አምባሳደር፣ “በመኖሪያ ቤታቸው ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤” ሲሉ፣ ያለተጨማሪ ዝርዝር መረጃ በቲዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት፣ ስለዚኽ ጥቃት አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያው ምላሽ አልሰጡም።

ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጊ ድርጅት የኾነው የሕፃናት አድን ድርጅት(Save the Children)፣ በመላው ሱዳን የሚያደርገውን አብዛኛውን እንቅስቃሴ በጊዜያዊነት አቁሟል። በዳርፉር የሚገኘው የተቋሙ ቢሮዎች መዘረፋቸውንና የሕክምና አቅርቦቶች፣ ተንቀሳቃሽ ኮምፒዩተሮች፣ ተሸከርካሪዎች እና ማቀዝቅዣዎች መዘረፋቸውንም አስታውቋል። የዓለም ምግብ ፕሮግራምም በተመሳሳይ፣ ሦስት ሠራተኞቹ፣ በዳርፉር መገደላቸውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ እንቃስቃሴዎቹን ማቋረጡን ገልጧል፤ ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴም እንዲሁ ሥራዎቹን አቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ በሱዳን ግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች፣ ክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። የድርጅቱ ዋና ሓላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም፣ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጤና ተቋማት እናራተኞቻቸው፣ በፍጹምላማ መኾን የለባቸውም፡፡ በተለይ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰላማውያን የድንገተኛ ጊዜ ክብካቤ በሚያሻቸው እንዲህ ባለ ወቅት፣ በጣም ግልጽ መኾን እፈልጋለኹ። ሁሉም ወገኖች፣ ጉዳት ለደረሰባቸውና የሕክምና አገልግሎት ለሚያስፈልገው ማንኛውም ሰውያልተገደበና ደኅንነቱ የተጠበቀ የጤና አቅርቦትን ማረጋገጥ አለባቸው፤” ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማት እየተዘረፉና በአንዳንድ አካባቢዎችም ለወታደራዊ አገልግሎት መዋላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እየወጡ መኾናቸውን ያመለከቱት ዶክተር ቴድሮስ፣ ሁሉም ወገኖች በዓለም አቀፍ ሕጉ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ጠይቀዋል። ዋና ሓላፊው አያይዘውም፣ የሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የ270 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ከ2ሺሕ600 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ማስታወቁን በመጥቀስ፣ የሱዳን ኹኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስገንዝበዋል፡፡ “በአሳዛኝ ኹኔታየዓለም ምግብ ፕሮግራም ሦስትራተኞችም ተገድለዋል። የሕይወት ማጥፋቱን ድርጊት ሁሉ አወግዛለኹ፡፡ ከሱዳን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ጋራም አብረን በአጋርነት እንቆማለን፤” ሲሉም አክለዋል፡፡

አሳሳቢው የሱዳን የተፋላሚ ኃይሎች ውጊያ የሚያደርሰውን አስከፊ ውድመት እና ሠቆቃ፣ አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ለመግታት፣ በአራት አህጉር(በስም ቢዘረዘሩ) ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እርቅ ለማውረድ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ፤ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም፣ ቀውሱን አስመልክቶ ሊወያይ ተዘጋጅቷል። /በተለያዩ የዜና አውታሮች የተሰናዱትን ዘገባዎች ወደ አማርኛ የመለሰቻቸው ስመኝስ የቆየ ናት።/

XS
SM
MD
LG