በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳን በመጪው ወር በሲቪል የሚመራ መንግሥት ልትመሠርት ነው


ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን
ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን

የሱዳን ወታደራዊ መሪዎችና የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ኃይሎች ከመጪው ሚያዚያ 3 ጀምሮ በሲቪል የሚመራ መንግሥት ለማቋቋም መወሰናቸውን ሁለቱንም ወገኖች የሚወክሉ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ የተደረሰው ሥምምነት መጋቢት 23 ቀን እንደሚፈረምና፣ ከቀናት በኋላም አዲስ የሽግግር ሕገ መንግሥት እንደሚፈረም ቃል አቀባዩ ካሊድ ኦማር በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በጥቅምት 2013 በጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት በምዕራባውያን ይደገፍ በነበረው መንግሥት ላይ ከተደረገ በኋላ ሱዳን ቀውስ ውስጥ ከርማለች። መፈንቅለ-መንግሥቱ የተደረገው አገሪቱን ለ 30 ዓመታት የገዙት ኦማር አል በሽር በአመጽ በተወገዱ በሁለት ዓመቱ ነበር።

በመጪው ሚያዚያ 3/2015 የሽግግር ሥልጣን ያላቸው ተቋማት መመሥረት እንደሚጀምሩ ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።

በሱዳን ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ የተደረሰው ሥምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ ግፊት ሲደረግ ቆይቷል። የጸጥታ ዘርፉን ማሻሻልና የሽግግር ፍትህን በሚመለከት አሁንም መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮች መሆናቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

ከዘጠኝ የዲሞክራሲ አቀንቃኞች፣ አንድ የጦሩ ተወካይ እንዲሁም አንድ አፋጣኝ ረዳት ኃይሎች ከተባሉት የተውጣጣው 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ የመጨረሻውን የሥምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጅ ሥራ ተሰጥቶታል።

አፋጣኝ ረዳት ኃይሎች የተባለውና በ10 ሺህ የሚቆጠር አባላት ያሉት ሠራዊት መሪ የሆኑት ጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሲቪል ሽግግሩ ሂደት ከፊት እንደሚሠለፉ ይጠበቃል። ዳጋሎ ከሌሎች የሠራዊቱ መሪዎች እራሳቸውን አግለው ከሲቪል ፖለቲካዊ ቡድኖች ጋር ተቀራርበው በመሥራት ላይ ሲሆኑ፣ ይህም ከሽግግር ሂደቱ በኋላም በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ዋና ተዋናይ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል ተብሏል። ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ፍጥጫ ዳጋሎ ሠራዊታቸውን ካርቱም ውስጥ ማሥፈራቸው ይታወቃል።

ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳዳር የምትመለስ ከሆነ ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ ተቋርጦ የነበረው ዓለም አቀፍ ዕርዳታና የገንዘብ ፍሰት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

XS
SM
MD
LG