ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአገሮችን የመብት አያያዝ የሚፈትሽበትን ዓመታዊ ሪፖርት ትላንት ይፋ አደረገ።
አምነስቲ በዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርቱ፣ የግፍ ግድያዎችንና ሕገ ወጥ እስሮችን ጨምሮ በዓመቱ ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ተፈጸሙ ያላቸውን መልከ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝሯል፡፡
ሪፖርቱ በቅድሚያ፣ “የፌደራል መንግሥት ለትግራይ የሚላከውን ሰብአዊ ርዳታ ማገዱን በመቀጠል፣ ከነሐሴ እስከ ኅዳር ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ አቅርቦቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ አደረገ፤” ሲል ይንደረደራል፡፡ “በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፣ የሕግ ጠበቃ ሳያገኙ እና ያለፍርድ መደበኛ ባልኾኑ የማቆያ ሥፍራዎች በዘፈቀደ ታስረው እንዲቆዩ ተደርገዋል፤” በማለትም ይቀጥላል።
“የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝ ተጥሶ እስር ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል፤” ያለው ሪፖርት አክሎም፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና የታጠቁ ቡድኖች፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የግፍ ግድያ መፈጸማቸውን፣ ይህም በአንዳንድ ኹኔታዎች ከጦር ወንጀል ሊቆጠር እንደሚችል ጠቁሟል።
“የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝ ተጥሶ እስር ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል፤”
መንግሥት፣ እነዚኽን በጦር ወንጀል ደረጃ የሚታዩ አድራጎቶች ለማጣራት የገባውን ቃል ሳይፈጽም መቅረቱን ያሰፈረው ሪፖርቱ፣ በአፋር ክልል ከግጭቱ ጋራ በተያያዘ በርካታ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች በትግራይ ኃይሎች ተፈጽመዋል፤ ሲል ህወሓትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ሪፖርቱ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትም በዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ መሸርሸሩን አመልክቷል። በበርካታ ዋና ዋና ርዕሶች ተከፋፍሎ የቀረበው የአምነስቲ ዘገባ፣ ለዘንድሮው ሪፖርቱ ዳራ ያደረገውን ያስቀድማል።
“የሰብአዊ አቅርቦት መከልከል”
የትግራዩ ግጭት ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በተለይም፣ ወደ አማራ እና አፋር መዛመቱን እንዲሁም፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት እና ሁከት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉን ገልጿል። አያይዞም፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በሌሎች ክልሎች ከተቀሰቀሱት ግጭቶች እንዲሁም፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋራ ተያይዞ በተከሠተው ድርቅ ሳቢያ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ለሰብአዊ ርዳታ ጥበቃ መጋለጣቸውን አስታውሷል፡፡
አምነስቲ፣ “የሰብዓዊ አቅርቦት መከልከል” በሚል ርእስ በአሰፈረው ዘገባ፣ ግጭቱ ከተጀመረበት እአአ ከኅዳር 2020 አንሥቶ፣ መንግሥት ለትግራይ በሚላከው የሰብአዊ ርዳታ ላይ እገዳ ጥሎ መቆየቱን፤ ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎም፣ ወደ ክልሉ የሚጓዙ ርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን፤ ኾኖም፣ ውጊያው ዳግም በማገርሸቱ፣ ካለፈው ዓመት ነሐሴ አንሥቶ የደቡብ አፍሪካው የሰላም ሥምምነት እስከተደረሰበት እስከ ኅዳር ወር 2023 ድረስ፣ የሰብአዊ አቅርቦቱ ዳግም ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ መቆየቱን ዘርዝሯል።
በክልሉ፣ የባንክ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች መዘጋታቸው፣ ሰብአዊ ቀውሱን ለማባባስ ተጨማሪ ምክንያት እንደነበር ሪፖርቱ ጠቅሷል። ከሥምምነት በኋላ ግን፣ የስልክ ግንኙነት እና ወደ ትግራይ የሚደረጉ የመንገደኞች የአየር በረራ መቀጠሉን አውስቷል።
የአምነስቲው ሪፖርት፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲያጤን የሰየመውን አጥኚ ኮሚሽን ዋቢ አድርጎም፣ መንግሥት ረኀብን እንደ ጦር ዘዴ ሲጠቀም ነበር፤ ብሎታል።
የዜጎች በዘፈቀደ መያዝ እና እስር
“በምዕራብ ትግራይ፣ በአፋር፣ በዐዲስ አበባ እና በአማራ በመሳሰሉ በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው የጅምላ እስር ከጦር ወንጀል ሊቆጠር ይችላል፤” ሲል መንግሥትን የወነጀለው የአምነስቲ ሪፖርት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ በይፋ ለዚኽ ዓላማ ባልተቋቋሙ እና መደበኛ ባልኾኑ የእስረኛ ማቆያዎች እንደኾነ፤ ይኸውም፣ የፍርድ ቤት ክትትል ሳይደረግባቸው እና የሚሟገትላቸው የሕግ ጠበቃም ባላገኙበት ነው፤” ብሏል።
“በምዕራብ ትግራይ፣ በአፋር፣ በዐዲስ አበባ እና በአማራ በመሳሰሉ በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው የጅምላ እስር ከጦር ወንጀል ሊቆጠር ይችላል፤”
በጥር ወር፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን፣ ሰመራ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ ስፍራ በኃይል በማዛወር ለወራት ማቆየታቸውን፤ ሰላማዊ ዜጎችን አስገድዶ ማዘዋወሩ ለደኅንነታቸው ታስቦ እንደኾነ የተሰጠው ምክንያት አሳማኝ እንዳልነበረና ቆይቶም የተፈጸመው የዘፈቀደ እስር፣ “ከጦር ወንጀል ሊቆጠር የሚችል ነው፤” ብሏል።
የአምነስቲው ሪፖርት በዚኹ ርእሰ ጉዳይ ሥር እንዳሰፈረው፣ መንግሥት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ከፍተኛ አመራር አባላት መሀከል፥ ሚካኤል ቦረን፣ ኬነሣ አያና፣ ገዳ ኦልጂራ፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ገቢሳ እና አብዲ ረጋሳ የተባሉ ግለሰቦችን፣ በሕገ ወጥ መንገድ አስሯል። በተደጋጋሚ የተሰጡ የፍርድ ቤት ትእዛዞች ተጥሰውም፣ ሰዎቹ ከ2020 ጀምሮ ታስረው መቆየታቸውን፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በግንቦት ወር የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ፣ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሠው፣ ለኹለት ዓመታት ያህል በእስር ላይ የቆዩትን ኮሎኔል ገመቹ አያናንና አንድ ሌላ የኦነግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ፖሊስ ከእስር መልቀቁን ጠቅሷል።
በተመሳሳይም፣ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከእስር እንዲፈቱ በመጠየቁ፣ እአአ ከግንቦት 2021 አንሥቶ እስከተለቀቁበት የመጋቢት ወር ድረስ፣ በቁም እስር ላይ እንደነበሩ አካቷል።
ከ30 ያላነሱ የተቃዋሚው “ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” ፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮችም፣ ፖሊስ፣ በመጋቢት እና በሚያዝያ ወር፣ በዐዲስ አበባ ሕዝባዊ በዓል በማክበር ላይ ሳሉ ማሰሩን፣ ከቀናት እስር በኋላም ክሥ ሳይቀርብባቸው መለቀቃቸውን፣ የአምነስቲው ሪፖርት ያዘክራል።
በሰኔ ወር፣ የባልደራስ ከፍተኛ አመራር አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ በባሕር ዳር መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ ትእዛዝ ቢሰጥም፣ ፖሊስ ወደ ዐዲስ አበባ አምጥቶ በእስር ላይ እንዲቆዩ ማድረጉንና በመጨረሻም፣ እስከተለቁቁበት የኅዳር ወር ድረስ፣ ወደተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ሲያዘዋውራቸው መቆየቱን አመልክቷል።
“ሕገ ወጥ ጥቃቶች እና ግድያዎች”
አምነስቲ፣ “ሕገ ወጥ ጥቃቶች እና ግድያዎች” በሚል በአሰፈረው ዘገባ ደግሞ፣ የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች፥ በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎች በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን መግደላቸውን አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ምርመራ እንደሚካሔድና ግድያዎቹን የፈጸሙ ወንጀለኞችም ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ቢገባም፣ እስከ አሁን ድረስ ግን ስለተባለው ምርመራም ኾነ መቀጠል ስለነበረበት የክሥ ሒደት አንዳችም ይፋዊ መረጃ አለመቅረቡን ሪፖርቱ ዘግቧል።
በዚያው በመጋቢት ወር፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ ሦስት ሰዎችን በቁመናቸው ሲያቃጥሉ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ መሰራጨቱን የጠቀሰው የአምነስቲ ዘገባ፣ በሰኔ ወር፣ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው የኦሮሞ ልዩ ዞን ተፈጸመ ያለውን የጅምላ ግድያ የሚያሳይ ሌላ የቪዲዮ ምስል በስፋት መሰራጨቱን፤ ቪዲዮው፥ የአማራ ታጣቂዎች ተኩሰው ሲገድሉዋቸው ማሳየቱንም የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።
ዓመታዊ ሪፖርቱ በመቀጠልም፣ በሰኔ ወር በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ፣ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በሚለው ታጣቂ ቡድን መኾኑ በተነገረለት ጥቃት፣ ሴቶች እና ሕፃናት የሚበዙባቸው ቁጥራቸው ከ400 የማያንስ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን አስታውሷል።
በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ጥቃቱን ለማስቆም ምንም ዓይነት ርምጃ ያለመውሰዳቸውን፤ በተከታዩ የሐምሌ ወር፣ በቄለም ወለጋ ዞን የዚኹ ታጣቂ ቡድን አባላት ሳይኾኑ እንዳልቀሩ የተጠረጠሩ ኃይሎች፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት መፈጸማቸው መዘገቡን ሪፖርቱ አውስቷል።
አያይዞም፣ በነሐሴ እና በመስከረም ወራት፣ የአማራ ፋኖ ታጣቂዎች እና የኦነግ የሸኔ ታጣቂዎች፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ “ፈጸሟቸው” ባላቸው ጥቃቶች፣ “በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች ተገድለዋል፤” ብሏል። በተጨማሪም በነሐሴ ወር የመጨረሻዎቹ ኹለት ቀናት(የቀን አቆጣጠሩ አሁንም በአውሮፓያኑ ነው)፣ የአማራ ፋኖ ኃይሎች፣ በሆሮ ጉድሩ አጋምሳ ከተማ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ “ከ60 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን ገድለዋል፤” ብሏል። በመስከረም ወር፣ እንደገና በሆሮ ጉድሩ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ እና የአማራ ንጹሐን ዜጎች፣ “በአማራ ፋኖ ታጣቂዎች እና በኦነግ ኃይሎች የአጠፌታ ጥቃት ተገድለዋል፤” ሲል ዘግቧል።
“በጥር ወር፣ የትግራይ ክልልን በምታዋስነው የአፋሯ የአባላ ከተማ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች፣ በትግራይ ኃይሎች፣ የአፋር ፖሊስ እና ሚሊሻዎች ተገድለዋል፤” ያለው የድርጅቱ ሪፖርት፤ አባላን ለመቆጣጠር በተደረገ ውጊያ፣ የአፋር ኃይሎች በከተማው ውስጥ የትግራይ ተወላጆችን ሲገድሉ፣ የትግራይ ኃይሎች በፈጸሙት የከባድ መሣሪያ ድብደባ ደግሞ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና ይህም ከጦር ወንጀል እንደሚቆጠር ገልጧል።
“በጥር ወር፣ የትግራይ ክልልን በምታዋስነው የአፋሯ የአባላ ከተማ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች፣ በትግራይ ኃይሎች፣ የአፋር ፖሊስ እና ሚሊሻዎች ተገድለዋል፤”
በሌላ በኩል፣ “በትግራይ የተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት አጥፍተዋል፤” ያለው ሪፖርቱ፣ የመንግሥታቱን ድርጅት ዘገባ ዋቢ አድርጎ፣ “የመንግሥት ኃይሎች፣ በጥር ወር፣ ደደቢት ላይ ፈጸሙት በተባለው የአየር ጥቃት፣ ከ100 በላይ ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል። በፌደራል ጦር እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎም፣ በነሐሴ እና በመስከረም ወር፣ በመቀሌ እና በዓዲ ዳዕሮ የአየር ጥቃት፣ ሕፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤” ብሏል። ነሐሴ 26 ቀን መቀሌ ላይ፣ በአንድ ሙዓለ ሕፃናት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት፣ ሕፃናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።
ሪፖርቱ አክሎም፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት መገደብ፣ በሚሉ ርእሶች በአሰፈረው ጽሑፍ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በዜጎች ላይ ተፈጸሙ ያላቸውን መጠነ ሰፊ በደሎች ዘርዝሯል።
አድማጮች፣ በአምነስቲ ሪፖርት የተጠቀማቸው ቀናት እና ወራት በሙሉ፣ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት የተጠቀሱ እንደኾነ በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን።