በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የተጀመረው ምርመራ መቀጠል እንዳለበት ተመድ ገለፀ


በኢትዮጵያ የተጀመረው ምርመራ መቀጠል እንዳለበት ተመድ ገለፀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:14 0:00

በኢትዮጵያ የተጀመረው ምርመራ መቀጠል እንዳለበት ተመድ ገለፀ

“በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ወቅት የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምርመራዎች መቀጠል አለባቸው” ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ያቋቋመው የምርመራ ቡድን አሳስቧል።

ቡድኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ምርመራ እንዲያካሂድ መንግስት እንዲፈቅድም ጥሪ አቅርቧል። "በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት አመታት የተካሄደውን አስከፊ ግጭት ለማስቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት በጦርነቱ ወቅት ደረሱ የተባሉትን የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ምርመራ ለማቆም ምክንያት አይሆንም" ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መርማሪ ቡድን አባላት አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክርቤት ማክሰኞ እለት በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ ባካሄደው ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ የተፈፀመውን የመብት ጥሰቶች እንዲያጣራ የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ዋና ኃላፊ መሀመድ ቻንዴ ኦትማን ባደረጉት ንግግር፣ እ.አ.አ በህዳር 2022 በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተፈረመው የሳልም ስምምነት "ወሳኝ እርምጃ" ነበር ያሉ ሲሆን፣ ከሰላም ስምምነቱ በፊትም ሆነ በኃላ ደረሱ የተባሉትን የመብት ጥሰቶች ማጣራት ዘላቂ ሰላም ሰላም ለማምጣት እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

"እ.አ.አ በ2022 ያወጣነው ሪፖርት ጦርነቱ እ.አ.አ በ2020 ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈፀሙ የሚያሳምኑ ምክንያቶችን አግኝቷል።" ያሉት መሀመድ ቻንዴ "ኮሚሽኑ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኃላ ተፈፅመዋል ከተባሉ ከባድ የመብት ጥሰቶች በተጨማሪም እነዚህን ክሶች ማጣራቱን ቀጥሏል። እንደዚህ አይነት ድርጊቶች በገለልተኛ ቡድን መጣራታቸው ከጥቃት ለተረፉት፣ ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ወደፊት ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እና ጉዳቶች እንዳይፈፀሙ ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑን ኮሚሽኑ ያሰምርበታል።" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሰፊ የመብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን አስታውቆ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት እና የኤርትራ አጋሮቹ እየተከሰቱ ባሉት የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ጀርባ እንዳሉ "ለማመን ምክንያታዊ መሰረቶች" እንዳሉት ገልጾ አስጠንቅቆ ነበር።

እ.አ.አ በ2021 መጨረሻ በመንግሥታቱ ድርጅት የተቋቋመው ሶስት አባላት ያሉት አጣሪ ቡድን የተሰጠው ተልዕኮ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ለሌላ ለአንድ አመት ታድሷል። ሆኖም እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፈቃድ እንዳላገኙ ያስረዱት ኦትማን "እስካሁን ድረስ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም የኢትዮጵያ መንግስት መርማሪ ቡድኖቻችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አልፈቀደም። በዛ ምክንያት አብዛኛው ስራችን በርቀት እየተካሄደ ነው። ስለዚህ መንግስት ከኮሚሽኑ ጋር ላለመተባበር ያሳለፈውን ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጠነው አጥብቀን እናሳስባለን።" ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድንን ጨምሮ በርካታ የመብት አቀንቃኝ ቡድኖች እና ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ምርመራውን ቀድማ ለማቆም እቅድ ያላት ትመስላለች በማለት ስጋታቸውን እየገለፁ ሲሆን ይህ አይነት እንቅስቃሴ በምክርቤቱ ትዕዛዝ በሚደረግ ምርመራ ላይ ታይቶ እንደማያውቅ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያሰበችውን የውሳኔ ሀሳብ ከማቅረቧ በፊት፣ ውሳኔውን የማሳለፍ እድል እንዲኖራት ቢያንስ ከ47 የምክርቤቱ አባል ሀገራት በቂ ድጋፍ ማግኘት ይኖርባታል።

ማክሰኞ እለት በተካሄደው የምክርቤቱ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ዳካ ግን ሀገራቸው ምርመራው ያለጊዜው እንዲቋረጥ ለማድረግ የነበራትን ሀሳብ ሳትተወው እንዳልቀረች አመላክተዋል። "ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን የመጨረሻውን ሪፖርቱን እስከሚያቀርብበት እስከ መስከረም ወር ባለው ጊዜ፣ በቅድመ ሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱትን አይነት የሰላም ስምምነቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ቀስቃሽ እና መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን ላለመድገም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።" ብለዋል። አባል ሀገራት በመጪው ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የምክርቤቱ ስብሰባ ድምፅ እንዲሰጥባቸው የሚፈልጓቸውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቦች እስከመጪው ሀሙስ ድረስ ማቅረብ ይጠብቅባቸዋል።

/ዘገገባው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስን ነው። ሙሉውን በድምፅና ምስል ለመከታተል የተያያዘውን ፋይል ይጫኑ/

XS
SM
MD
LG