"ከዚህ ምድር እናጠፋችኃለን- በኢትዮጵያ ምዕራብ ትግራይ ዞን በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል እና ዘር ማፅዳት" በሚል ርዕስ ዛሬ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ሂዩማን ራይትስ ወች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጡት 240 ገፅ የጋራ ሪፖርት፣ በምዕራብ ትግራይ አዲስ የተሾሙ ባለስልጣናት እና የአጎራባቹ አማራ ክልል የፀጥታ ሀይሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ሰፊ እና ስልታዊ ጥቃት በማድረስ በመቶ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ከመኖሪያቸውእንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውን አስታውቋል።
በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ባለስልጣናት የሰብዓዊ መብት ርዳታ፣ የመንቀሳቀስ መብት፣ በትግርኛ ቋንቋ መናገርን እና የማረስ መብትን መከልከላቸውን የሚገልፀው ሪፖርት የአማራ የፀጥታ አካላት እና በአንድ አንድ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ደግሞ የኤርትራ ሀይሎች፣ እህል፣ ከብቶችና መሳሪይዎችን በመዝረፍ የትግራይ ተወላጆችን ማሰቃየታቸውንአብራርቷል። የኤርትራ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም።
የአምነስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ በምርመራ ያገኟቸውን መረጃዎች እንዲህ ያብራራሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ያናገሯት ባእከር በተባለ ከተማ ትኖር የነበረች የትግራይ ተወላጅ ሴት 'ፋኖ' ስትል የገለፀችውኢመንደበኛ የአማራ ሚሊሺያ አባላት አደረሱብኝ ያለችውን ማስፈራሪያ ስትገልፅ "እንገላችኃለን፣ ከዚህ አካባቢ ውጡ" የሚል የትግራይ ተወላጆች በ24 ሰዓታት ውስጥ ወይም በ72 ሰዓታት ውስጥ ለቀው ካልወጡ እንደሚገደሉ የሚገልፅ በራሪ ወረቀት በየምሽቱ ይበተን እንደነበር ገልፃለች።
በሱዳን ስደት ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን እና በትግራይ እና በአማራ ክልል የሚኖሩ ተጎጅዎችን እንዲሁም የአይን እማኞችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎችን ማናገራቸውን የሚጠቅሱት የሂዩማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር በበኩላቸው ጥናቱ ከአንድ አመት በላይ በሆነ ግዜ ውስጥ በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ የመብት ጥሰቶችን እንዳካተተ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የዛሬው ሪፖርት ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ ከተማ የትግራይ ሚሊሺይዋዎች እና ነዋሪዎች በአማራ ተወላጆች ላይ አካሂደውታል ያለውን የመጀመሪያ ከፍተኛ ጭፍጨፋና የጦር ወንጀል መፈፀማቸውን ያስታወሰ ሲሆን ከዛ በኃላ ባሉት ግዜያት የአማራ ተወላጆች በቀል መፈፀማቸውን አቶ ፍሰሃ ገልፀዋል።
የምዕራብ ትግራይ አካባቢ ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ድምበር እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ሲካሄዱበት መቆየቱን የዛሬው ሪፖርት ጠቅሷል። አቶ ፍሰሃም በሁለቱ ህብረተሰቦች መሀከል የነበረው ግጭት ሳይፈታ መቆየቱ ለዛሬው ችግር እንደመነሻ ሊታይ ይችላል ይላሉ።
የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ በአሰባሰቧቸው የመብት ጥሰት መረጃዎች ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም የአማራ እና የትግራይ ክልል አመራሮች መልስ እንዲሰጡበት ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር የገለፁት አቶ ፍሰሃ ምላሽ ያገኙት ከአማራ ክልል ብቻ መሆኑን ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ዛሬ ይፋ በተደረገው ሪፖርት ተፈፀሙ ተብለው የተገለፁት ወንጀሎች እውነታውን የማያንፀባርቁ፣ ላንድ ወገን ያደሉ ወንጀል ፈፅመው በሱዳን የተሸሸጉ የህወሃት ሰዎችን በመረጃ ምንጭነት የተጠቀመ እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ሲሉ በጎንደር ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መምህር ጌታ አስራደው ተችተውታል።
መምህር ጌታ አስራደው በጎንደር ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ ከአንድ አመት ከሶስት ወር በላይ ደግሞ የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበት ወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢ የጎንደር ዩንቨርስቲ ባደራጀው የምሁራን የጥናት ቡድን መሪ ናቸው። ከቀናት በፊት ዩኒቨርስቲው ይህንን አካባቢ በመተመለከተ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን ከአማራ ክልል ምላሽ ለማግኘት ያድረግነው ጥረት ባለመሳካቱ መምህር ጌታ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል።
የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ ያወጡት ሪፖርት በማጠቃለያው በምዕራብ ትግራይ የሚኖሩ ንፁሃን ዜጎችን ለመጠበቅ በአካባቢው ያሉ ሚሊሺዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራ የሰላም አስከባሪ ሀይል በቦታውእንዲሰማራ መጠየቃቸውን ላቲሺያ ይገልፃሉ።
ሂዩማን ራይትስ ወች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፣ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ "በዚህ ሪፖርት ላይ የተጠቀሱት፣ በማይካድራ የትግራይ ሚሊሺያና ፖሊስ ሳምሪ ተብሎ ከሚጠራ ቡድን ጋር በአማራ ተወላጆች ላይ የፈፀሙት ግድያዎች እና በግዳጅ ማፈናቀል እንዲሁም ከዛ በኃላ የተፈፀሙ የበቀል ጥቃቶች፣ የአማራ ልዩ ሀይሎች፣ ሚሊሺያ እና ፋኖ ቡድኖች የትግራይ ተወላጆች ላይ ያደረሱት ህገወጥ ማፈናቀል" በአጠቃላይ በሪፖርቱ ላይ የተካተቱት የመብት ጥሰቶች ኮሚሽኑ በግሉ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ጋር በጋራ ካወጧቸው ግኝቶች ጋር የሚመሳሰልነው ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ አክለው ተጨማሪ ማፈናቀሎች እንዳይፈፀሙ ርምጃዎች እንዲወሰዱ እና ከአካባቢያቸው በጉልበትየተፈናቀሉ ሰዎች በፈቃደኝነት መመለስ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ እንዲሁም የወልቃይት እና ጠገዴ የኖረ የመሬት ግጭት ቋሚ መፍትሄ እንዲያገኝ በሚል በጥምር ሪፖርቱ ላይ የተሰጠው ምክረ-ሀሳብ ተፈፃሚ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ ላወጡት ሪፖርት ማምሻውን ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በሪፖርቱ የተዘረዘሩትን የዘር ማፅዳት፣ የጦር ወነጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች በጥልቀት እንደሚመረምረው አስታውቋል።
ሪፖርቱ በቅርቡ በሀገሪቱ የተፈፀሙ ፖለቲካዊ ለውጦችን፣ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የውስጥ ወሰን ጉዳዮችን እንደሚዳስስ መመልከቱን የገለፀው የመንግስት መግለጫ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱትንና የሰብዓዊነት ህግጋትን የጣሱትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ፣ ለዚህም ግብረሀይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ሆኖም በህገ መንግስቱ መታየት ባለባቸው የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ዙሪያ ጣልቃ መግባት ተገቢ አይደለም ሲል የገለፀው የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ ይህ ሪፖርቱን ለፖለቲካ አላማ መጠቀሚያ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። የተዘረዘሩት ጥቃቶች ለአንድ ወገን ያደሉ መሆናቸው ጥላቻን የሚያባብስ እና ዕርቅ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ጨምሮ አስታውቋል።