ለሁለት አመታት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በተደረገው ጦርነት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ፍትህ እንዲያገኙ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ሊያሳድር ይገባል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ጥሪ አቀረበ።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሚሰሩት ሱዓድ ኑር፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ ለደረሰው ጥቃት ተጠያዊነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
"ስለሰላም ስናወራ፣ የሰላም መሰረቱ ፍትህ እና ተጠያቂነት ነው። ስለዚህ ፍትህ እና ተጠያቂነት ለውይይት ሳይቀርብ ስለሰላም ልናወራ አንችልም። ስለዚህ ስለሰላም ከማውራታችን በፊት መነሻው እሱ ሊሆን ይገባል።"
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊት፣ ሚሊሺያዎች እና የትግራይ ኃይሎች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያሳይ ዘመቻ በዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሯል።
በናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆ በተመራው የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሁለቱ ተዋጊ አካላት ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል። ሆኖም የመብት ተሟጋቹ ቡድን ሂደቱ ለተፈፀሙት የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነት የሚያሰፍን ፍኖተ-ካርታ ሊያስቀምጥ ይገባል ብሏል። ተፋላሚ ቡድኖቹን በንፁሃን ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስም ይከሷቸዋል። ቡድኖቹ ግን ይህን አይቀበሉም።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሚሰሩት አቶ ፍሰሃ ተክሌ እንደሚሉት ለሁለት አመት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን በደል ለማጣራት ሰብዓዊ መብት መርማሪ ቡድኖች ያልተገደበ ተደራሽነትን ይፈልጋሉ።
"አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወደ አካባቢው ለመሄድ በርካታ ግዜ ጥያቄ አቅርቧል። ነገር ግን ለጥያቄያችን ምላሽ አልተሰጠንም። አሁን የምንጠይቀው የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲመዘገቡ ነው። በግጭቱ የተፈፀሙ ጥሰቶችን መዝግቦ ለመጨረስ ገና ብዙ ይቀረናል። ስለዚህ ያንን ለመጨረስ እና እውነቱን ለማውጣት የመጀመሪያው ርምጃ፣ ለገለልተኛ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ተደራሽነትን መፍቀድ እና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።"
በዚህ ወር መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ላይ ግፊት ለማድረግ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ ኦባሳንጆ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌን ጎብኝተው ነበር።