በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ወታደሮች ሲንገላታ የሚያሳየውን ታዳጊ ቪዲዮ ጉዳይ እየመረመረ መሆኑን የመብቶች ኮሚሽኑ ገለፀ


የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢንተርኔት እየተዘዋወረ ያለውን የመንግሥት ወታደሮች አንድ የትግራይ ተወላጅ ወንድ ልጅ ሲያንገላቱ ከዚያም በጥይት ሲመቱ የሚያሳይ የሚመስል የቪድዮ ምስል በመመርመር ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የአራት ደቂቃ ርዝማኔ ባለው የቪዲዮ ምስል ላይ አንድ ወጣት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መለዮ ልብስ በለበሱ ሰዎች ተከብቦ ተቀምጧል፥ የትግራይ ተወላጅ የሆነውን ወጣት አቢ አዲ ከተባለ የሰሜን ትግራይ አካባቢ ነው የመጣው በማለት ሲያዋክቡት ይታያል።

ጉዳዩን በተመለከተ ቪኦኤ የጠየቀው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ገልጿል።

በቪዲዮ ምስሉ ፊቱ ላይ ደም የሚታየው ወጣቱ ቁጭ እንዳለ የከበቡት ዩኒፎርም የለበሱ ወንዶች እንገድልሃለን እያሉ ያስፈራሩታል። ከመካከላቸው አንደኛው አሁን መገደል የለበትም መሰቃየት አለበት ይላል። አንዲት ታዳጊ ሴት ልጅን ምግብ አስገድዳ እንድታበላው ይነግሯታል።

ከዚያም ከመካከላቸው አንደኛው ቀረብ ብሎ ሲተኩስበት ነው የቪዲዮ ምስሉ የሚያበቃው። ቪኦኤ ይህ ሁኔታ የተከሰተበትን ስፍራም ሆነ በምስሉ ላይ የሚታዩትን ሰዎች ማንነት በነጻ ምንጭ ለማረጋገጥ አልቻለም።

ጉዳዩን አስመልክቶ የተጠየቁት የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

እአአ ባለፈው 2021 ጥር ወር ውስጥ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት ማዕከላዊ ትግራይ ማኅበረ ደጎ በሚባል ስፍራ ሲቪሎችን ሲገድሉ የሚታዩበት ተመሳሳይ ድንገት በመብት ተሟጋች ቡድኖች ሪፖርት መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን አምነስቲ እንተርናሽናል አስራ አንድ ሲቪሎች መገደላቸውን አረጋግጧል።

የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (ህወሓት) ተዋጊዎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊት በመፈጸም ተወንጅለዋል። እአአ በዘንድሮ 2022 የካቲት ወር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት የህወሓት ኃይሎች እና ተባባሪዎቻቸው በያዟቸው የአማራ ክልል ከተሞች ከአስራ ሁለት በላይ ሰዎች መግደላቸውን እና ሴቶችን እየተፈራረቁ መድፈራቸውን አመልክቷል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ካለፈው ዓመት ኅምሌ ወር እስከ ዘንድሮ መጋቢት ወር በነበረው ጊዜ ውስጥ ከትግራዩ ጦርነት በተያያዘ ከ740 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ህወሓትም በውጊያ እንቅስቃሴዎቻችን ሲቪሎችን ዒላማ አናደርግም በማለት የመብት ጥሰቶች ይፈጽማሉ የሚሉትን ክሶች ያስተባብላሉ።

“የኤዲተሩ ማስታወሻ:-

በዚህ ዘገባ ላይ የተገለፀውን አድራጎት ይበልጥ በሚገልፅ ቃል ለመተካት ርእሱ መቀየሩን እናስታውቃለን።

XS
SM
MD
LG