በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመቀሌ ከተማ የአየር ጥቃት ተፈፀመ


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ ከተማ

በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ላይ “የአየር ጥቃት ተፈፅሟል” ሲሉ የሆስፒታል ኃላፊዎች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። በጥቃቱ አንድ ሰው እንደተጎዳም ታውቋል።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ውጊያ ውስጥ ያለው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ካለ ቅድመ ሁኔታ በአፍሪካ ህብረት ለሚመራ የሠላም ንግግር ፈቃደኛ መሆኑን ካስታወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ መሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ለህወሓት ጥሪ መልስ ባይሰጥም፣ ካሁን ቀደም በሚሰጣቸው ኦፊሴላዊ መግለጫዎች ግን ካለምንም ቅድመ ሁኔት ወደ ሰላም ሂደት ለመግባት ፈቃደኛነቱን ሲያሳይ ቆይቷል።

የአይደር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብሮም ገብረስላሴ፣ በዛሬው የአየር ጥቃት የተጎዳ ያሉትን አንድ ሰው መቀበላቸውን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ተጎጂውን ይዞ ወደ ሆስፒታሉ የመጣ ግለሰብ፣ "የአየር ጥቃቱ የድምፀ ወያኔ ቴሌቭዥን ጣቢያን እና መቀሌ ዩኒቨርስቲን መምታቱን ነግሮኛል" ሲሉ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መግለፃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

“የድሮን ጥቃት ሃዲ ሃቂ የተባለ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አካል የሆነን ግቢ ኢላማ አድርጓል” ሲሉ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

ከኢትዮጵያ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና ከመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ አስተያየት ለማግኘት ሞክሮ እንዳልተሳካለት ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል

ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ጦርነቱ ካገረሸ ወዲህ የአየር ጥቃት ሲፈጸም ለሦስተኛ ግዜ ነው። ለጦርነቱ እንደገና መጀመር አንዱ ወገን ሌላውን ይወነጅላል።

የአፍሪካ ህብረትን በመወከል ሁለቱን ወገኖች ለማሸማግል ሲሰሩ የቆዩት የቀድሞው ያናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሲጉን ኦባሳንጆ ከአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር ጋር ትናንት ሰኞ መነጋገራቸውን፣ በስብሰባው ላይ ታድመው እንደነበር የገለጹት በኢትዮጵያ የቀድሞ የጂቡቲ አምባሳደር ሞሃመድ እድሪስ ፋራ በትዊተር ገፃቸው ጽፈዋል።

XS
SM
MD
LG