በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ተወላጆች ላይ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመውና “አሰቃቂ” ብሎ የገለጸው ግድያ እንዲመረመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ


በአማራ ተወላጆች ላይ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመውና “አሰቃቂ” ብሎ የገለጸው ግድያ እንዲመረመር
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:23 0:00

በአማራ ተወላጆች ላይ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመውና “አሰቃቂ” ብሎ የገለጸው ግድያ እንዲመረመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

ከ400 በላይ የአማራ ተወላጅ ሲቪሎች ባለፈው ወር በኦሮምያ ክልል የተገደሉበት ሁኔታ እንዲመረመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ሃሙስ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ድርጅቱ ጥሪውን ያቀረበው ድርጊቱን የፈጸሙት በክልሉ የሚገኙና ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው የሚጠሩ፣ መንግስት ደግሞ “ሸኔ” ብሎ የሚገልጻቸው ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ የተናገሩትን በአካባቢው የሚገኙ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ነው።

ሁከት እየተባባሰ በመጣበት የምዕራብ ወለጋ አካባቢ ሰኔ አስራ አንድ ቀን በአማራ ተወላጆች ላይ ለተፈጸመው ጭፍጨፋ መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራውና ራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚገልጸውን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርግ፥ ታጣቂው በበኩሉ ከመንግስት ጋር ያበሩ ሚሊሺያዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው ዘጠኝ የዓይን እማኞች እንደሚሉት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በቶሌ ቀበሌ ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመረው ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ነበር።

ገና የመጀመሪያው ጥይት እንደተተኮሰ ነዋሪዎቹ ለአካባቢው ባለስልጣናት ቢያሳውቁም፣ የመንግስት ሃይሎች የደረሱት ጥቃቱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ መሆኑን እማኞቹ ለአምነስቲ ተናግረዋል።

አጥቂዎቹ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ እንደጨፈጨፉ፣ ንብረት እንደዘረፋና ቤቶችን እንዳቃጠሉ ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ይህንን ድርጊት በሳተላይት ምስሎች ማረጋገጡን ገልጿል። ምስሎቹ እሳት በአካባቢው እንደነበር ያሳያሉ ብሏል አምነስቲ።

ዲፕሮሰ ሙቼና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሃላፊ ሲሆኑ፣ “ይህ በቶሌ በተጠርጣሪው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የተፈጸመው ሰቅጣጭ ግድያ ፈጻሚዎቹ ለሰው ህይወት ግድ እንደሌላቸው ማሳያ ነው። ይህ የሴቶችንንና የህጻናትን ህይወት የቀጠፈ ጭቃኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን በሚገባ መመርመር አለበት” ብለዋል።

የአምነስቲ መግለጫ የወጣው ባለፈው ወር የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ምሼል ባቼሌት የኢትዮጵያ መንግስት በቶሌ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ “ፈጣን፣ ገለልተኛና ጥልቀት ያለው” ምርመራ እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

የ64 ዓመቱ ሁሴን ለአምነስቲ እንደተናገሩት 22 ልጆችና የልጅ ልጃቸውን በጥቃቱ ተነጥቀዋል።

“በአንድ ቦታ ብቻ 42 ሰዎች ገደሉ። ከነዚህ ውስጥ አንድ ወንድ አዋቂ ብቻ ነው የነበረው፣ ሌሎቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው” ናቸው ብለዋል ሁሴን።

ሌላኛው የዓይን እማኝ ደግሞ፣ “የአንድ ጎረቤቴን ቤት፣ ቤተሰቡ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ውስጡ እያሉ በእሳት አጋይተውታል። አንዷ የሰባት ወር እርጉዝ ስትሆን ከሁለት ልጆቿ ጋር ነበረች። ከሰል እስኪሆኑ ስለተቃጠሉ እዛው ግቢ ውስጥ ቀበርናቸው” ሲሉ ለአምነስቲ ተናግረዋል።

የዓይን እማኞቹን ከበቀል ለመከላከል አምነስቲ እውነተኛ ስማቸውን በሚስጥር ይዟል።

የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ እስከአሁን ኦፊሴላዊ ቁጥር ባይቀመጥም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቃል አቀባይ ቢልለሌ ስዩም ባለፈው ወር በሰጡት መግለጫ 338 ሰለባዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።

አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ቢያንስ 450 ሰዎች መገደላቸውን ለአምነስቲ ተናግረዋል።

የዓይን እማኞቹ እንዳሉት አጥቂዎቹ በለበሱት መለዮ፣ በተሰሩት “ለየት ያለ ረጅም ሹሩባ” እና በሚጠቀሙት የኦሮምኛ ቋንቋ መሰረት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባል መሆናቸውን መለየት እንደቻሉ ተናግረዋል።

አጥቂዎቹ በተጨማሪም ቤቶችን ሲያቃጥሉ፥ ከብቶችን፣ ግንዘብና ሌሎች ንብረቶችን ከመንደርተኛው ዘርፈዋል።

ባለስልጣናት “መንገድ በመዘጋቱ መድረስ አልቻልንም” ማለታቸውን የአምነስቲ መግለጫ ጠቅሷል።

ባለስልጣናት በተጨማሪም በአማራ ተወላጆች ላይ ለተፈጸሙት በርካታ ጥቃቶች “ሸኔ” ብለው የሚጠሩት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ከ2010 ጀምሮ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ሲዋጋ የሰነበተው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፥ በሰሜን ኢትዮጵያ ከመንግስትና ሌሎች ሃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከነበረው ህወሃት ጋር ባለፈው ዓመት የትግል አጋርነት በማወጁ ትኩረት አግኝቷል።

[ዘገባው የኤ.ኤፍ.ፒ ዜና ወኪል ነው]

XS
SM
MD
LG