በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር ብቸኛው ሪፈራል ሆስፒታል የምግብ እጥረት ተጠቂዎች ለማዳን እየተፍጨረጨረ ነው


በአፋር ብቸኛው ሪፈራል ሆስፒታል የምግብ እጥረት ተጠቂዎች ለማዳን እየተፍጨረጨረ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:32 0:00

በአፋር ብቸኛው ሪፈራል ሆስፒታል የምግብ እጥረት ተጠቂዎች ለማዳን እየተፍጨረጨረ ነው

በኢትዮጵያ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው ድርቅ በሰሜናዊው አፋር ክልል የሚገኙ ህፃናት ላይ እያስከተለ ያለው የምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሄዶ በክልሉ ወደሚገኘው ብቸኛ ሪፈራል ሆስፒታል የሚገቡ ህፃናት በሰዓታው ውስጥ ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ሆስፒታሉ አስታውቋል።

ሀገሪቱ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ባካሄደችው ጦርነት ምክንያት በክልሉ ከሚገኙ ጤና ጣቢዎች ከአስር ከመቶ ያነሱት ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የቀሩት ሆስፒታሎች ችግሩን ለመቋቋም እየተፍጨረጨሩ ነው።

በኢትዮጵያ አፋር ክልል በብቸኝነት የሚያገለግለው ሪፈራል ሆስፒታል እንዳስታወቀው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ በከፍተኛ ሁኔታ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ 369 ህፃናት ወደ ሆስፒታሉ ገብተዋል።

ከአንድ ሚሊየን በላይ በሚኖርበት ክልል ሁለት የህፃናት ሀኪሞች ብቻ ያሉት ይህ ዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታል እጅግ በደከሙና ተስፋ በቆረጡ እናቶች ተጨናንቋል።

የአይና ከድር የአንድ አመት ልጅ ለምሳሌ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በምግብ እጥረት ለተጎዱ ማገገሚያ የሚሰጠውን ምግብ ሲወስድ ቆይቷል።

በምግብ እጥረት የተጎዳው ህፃን እናት አይና ከድር "ወደዚህ ስንመጣ ምግብም አይበላም ውሃም አይጠጣም ነበር። ይሞትብናል ብለን ፈርተን ነበር።"ይላሉ።

በአፍሪካ ቀንድ በአርባ ዓመታት ግዜ ውስጥ ያልታየው ድርቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖችን ለረሃብ እና ለምግብ እጥረት በሽታ አጋልጧል።

የተባበሩት መንግስታት እንዳስታወቀው በአፋር ክልል በምግብ እጥረት ምክያት ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ህፃናት ቁጥር በመጋቢት ወር ላይ በሰላሳ ከመቶ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ሲሆን እንደገነ በሚያዚያ ወር በ28 ከመቶ ጨምሯል።

የዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ተጠባባቂ ሀላፊ ዶክተር ሙሃመድ ዩሱፍ፣ በወር አምስት ህፃናትን ይቀበል የነበረው ሆስፒታል አሁን በቀን ብቻ አምስት ህፃናትን መቀበል እንደጀመረ ይገልፃሉ።

ዶክተር ሙሃመድ ዩሱፍ የዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ኃላፊ ናቸው፤ "ወደዚህ የሚመጡት ህመምተኞቹ በጣም ከደከሙ በኃላ ነው። ስለዚህ አብዛኞቹ ህመምተኞች በተቀበልናቸው በሁለት ወይም በሦስት ሰዓታት ውስጥ ይሞታሉ። ምክንያቱም የምግብ እጥረት ብቻ አይደለም ችግሩ፣ ብዙ ነገሮች ውስብስብ ናቸው። እንደ የሳምባ ምች፣ ደም ማነስ እና የተቅማጥ በሽታ አይነት ተያያዥ ችግሮች አሉባቸው።"

ከትግራይ ኃይሎች ጋር በተደረገው ጦርነት በአፋር ክልል ክልል የሚገኙ ክሊኒኮች መዘረፋቸውን፣ መውደማቸውን እና በአሁኑ ወቅት አገልግሎት የሚሰጡት ከ10 ከመቶ በታች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይገልፃሉ።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ሰዎች ወደ ዱብቲ አይነት ሆስፒታል እንዲመጡ የሚያስገድዳቸው ሆስፒታሉን ያጥለቀለቁት ታካሚዎች በየመተላለፊያ ኮሪደሩ ላይ እና በረንዳዎች ላይ ተኝተዋል - ከነዚህ የሚበዙት ደግሞ ህፃናት ናቸው።

አሚና አዳም ኢብራሂም የአንድ የታካሚ ህፃን እናት ሲሆኑ "ያስለዋል፣ ከፍተኛ ትኩሳት አለው፣ ምግብም አይበላም። ምን እንደሆነ ችግሩ አላወቅንለትም።" ይላሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ርዳታ ተቋማት በበኩላቸው ለጤና አገልግሎት የሚያስፈልገውን ለማሟላት እየተፍጨረጨሩ መሆኑን ይገልፃሉ።

"በአፋር ውስጥ የወደሙት የጤና ጣቢያዎች እንደገና እንዲቋቋሙ ወይም ለጊዜው የሚሆኑም ቢሆን አዳዲስ እንዲሰሩ ያስፈልጋል። አሁን ለማድረግ እየሞከርን ያለነው እሱን ነው። ግን ልል የምችለው አለመታደል ሆኖ በምንፈልገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን ነው። ግን በእቅዳችን ውስጥ ነው እናም እየተከታተልነው ነው።" ያሉት ደግሞ ማይክል ሳድ የተባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የዱብቲ ሆስፒታል ሀላፊ ዶክተር ዩሱፍ አንዳንድ የሆስፒታሉ ሰራተኞች በሁኔታዎች ተስፋ ቆርጠው ጥለው በመሄዳቸው የቀሩት ሰራተኞች ያለውን ሁኔታ ለመቋቋም አዳጋች እያደረገባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

XS
SM
MD
LG