በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የትግራይ ግጭት በኦሮምያ ክልል በፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን “ያልተቋረጠ የጥቃት አዙሪት እንዳይታይ ሸፍኗል” ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባም ዋና መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ምዕራብ ኦሮምያን ጨምሮ በነዋሪው ሕዝብ ብዛት ትልቁ በሆነው የኦሮምያ ክልል በአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት (እንደ ቡድኑም ገለጣ “የከፋ” ባለው) በአማጺያኑ ላይ የሚያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ሲቪሎችን የውጊያው ተጋላጭ አድርጓል።
ጥቅምት 2013 ዓ.ም በፌዴራል መንግሥት ኃይሎች እና በትግራይ ክልል አማጽያን መካከል የተቀሰቀሰውን መጠነ ሠፊ ውጊያ ተከትሎም ዓለም ትኩረቱን በትግራይ ላይ ባደረገበት ሁኔታ በኦሮምያው ያለው ግጭት ያለ አንዳች ሁነኛ መፍትሄ ለዓመታት ቀጥሏል፤ ብሏል።
ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አክሎም “በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ጨምሮ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አስቀድሞ በኦሮምያ ክልል ሲካሄዱ የቆዩ የመብት ረገጣዎች ተጠያቂነት ወይም ቅጣት በሌለበት ሁኔታ ሲፈጸሙ ነበር” ብሏል።
"ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የመብት ጥሰቶች አሁንም እንደ ቀጠሉ ናቸው። እናም አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት ይሻሉ።" ሲል አክሏል።
ይህ “ተጠያቂነት የሌለበት” ወይም “ወንጀል ፈጽሞ ያለመከሰስ” ባህል “ለፈጸሙት በደል ተጠያቂ የማይደረጉ የጸጥታ ኃይሎችን ይበልጥ ከማበረታታት ውጭ፣ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የፈየደው አንዳችም የለም።" ብሏል።
በየኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ራሱን የኦሮሞ ነጻ አውጭ ሠራዊት ብሎ በሚጠራው እና መንግስት በበኩሉ “ሸኔ” በሚለው ቡድን የገጠመውን አመጽ ለዓመታት ሲዋጋ ከቆየበት ምዕራብ ኦሮምያ ለመድረስ ያለው ዕድል ውሱን ነው።
“ሆኖም በመንግሥት ኃይሎች የሚፈጸም ግድያ እና የዘፈቀደ እስር አሁንም ድረስ መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሰባስቤያለሁ” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች “የአካባቢ መሪዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት በታጣቂው ቡድን መታፈን እና ግድያዎች እንደተፈጸመባቸው የሚረጋግጡ ማስረጃዎችም በተመሳሳይ ማሰባሰቡን አመልክቷል።
በሰኔ ወር ውስጥ በምዕራብ ኦሮሚያ ቶሌ በተባለች መንደር በመቶዎች የተቆጠሩ፣ አብዛኞቹም የአማራ ብሄር ተወላጆች የሆኑ ንጹሃን በታጣቂዎች መጨፍጨፋቸውን ያስታወሰው የኤፍፒ ዘገባ
“የአካባቢው ባለሥልጣናት ታጣቂው ቡድን ተጠያቂው ነው” ቢሉም ታጣቂው ቡድን በበኩሉ “የፈጸምኩት ነገር የለም” ሲል ውንጀላውን አስተባብሎ በፊናው የመንግስት ደጋፊ ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
ከሳምንታት ቀደም ብሎ የመንግሥት ኃይሎች በአጎራባቹ የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በደረሰ ጥቃት በታጣቂው ቡድን ግብረ አበርነት የጠረጠሯቸውን ሰዎች ያለ ፍርድ በመግደል መከሰሳቸውንም ዘገባው ጠቅሷል።
በወቅቱ በነበረው መንግሥት ላይ ብዙዎች የነበራቸውን ቁጣ እና ብስጭት ባንጸባረቁ የሙዚቃ ሥራዎቹ ይታወቅ ከነበረው የኦሮምኛ ዘፈኖች አቀንቃኝ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ወዲህ የኦሮምያ ክልል የበርካታ ግጭቶች መናኸሪያ ሆኖ መቆየቱንም አስታወሷል።
የሃጫሉን ግድያ ተከትሎም በተቀሰቀሰው ግጭት ከ160 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ መንግሥት በወሰደው መጠነ ሠፊ የኃይል እርምጃ ደግሞ በርካታ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት እና የተቃውሞ መሪዎች ተይዘው መታሰራቸውን አውስቷል።
“ቆይቶም ብዙዎች ከእስር ቢለቀቁም፤ አንዳንዶቹ ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ካዘዘም በኋላ እስካሁን አልተፈቱም” ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ተችቷል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ በመላው ኦሮምያ እየተባባሱ የመጡትን እነኚህን ቤተሰቦችን ለከፋ ስቃይ የዳረጉ ጥቃቶች ችላ ሊሉ አይገባም። በኃይል እርምጃዎች በሚመራው የጸጥታ አደረጃጀት ላይ የሚደረግ መዋቅራዊ ማሻሻያ እና ማኅበራዊ ጥገናም ያስፈልጋል።"
ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ "መንግሥት የተለያዩ ማኅበረሰቦች ባቀረቧቸው ጥሪ መሰረት በገዛ ኃይሎቹም ሆነ በታጣቂዎች በተፈጸሙት እና እየደረሱ ባሉት ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ላይ ተዓማኒነት ያለው ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ በማመቻቸት መጀመር ይችላል።" ሲል መግለጫውን አጠቃሏል።