የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በምዕራብ ኦሮሚያው ግጭት ባለፉት 15 ቀናት ብቻ ከ10ሺህ በላይ ሰው መፈናቀሉን ገለፀ፡፡
የግጭቱ ተጎጂዎች የተሰደዱት የተሻለ ደህንነት ወዳላቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ከ3 እና አምስት ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ ወደ አማራ ክልልም በብዛት እየገቡ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
አሁንም በጉዞ ላይ ያሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም ግጭት ካለባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል ከገቡት መካከል አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምጽ የሰጡ ተፈናቃዮች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ የተፈናቃዮች ቁጥር ጫና እየፈጠረበት መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል የምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የጊዳ አያና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ቶሌራ “ ግጭት ካለባቸው የዞኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ30 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በወረዳዉ ባሉ መጠለያዎች ይገኛሉ።” ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑንም ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተሻሻለ መሆኑን እና በአፋርና በአማራ ክልሎች በኩል ባሉ በአራት ኮሪደሮች ድጋፍ እየገባ መሆኑን ኦቻ ገልጿል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ