በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቡሩንዲ የፖለቲካ ንግግር ዘገየ ሁከቱ ተባብሷል


የእጅ ቦምብ ጥቃቶች እና ግድያዎቹ እንደቀጠሉ በመሆኑ የሰላም ንግግር ጥረቶችን ይበልጡን እየተወሳሰበ መጥቷል
የእጅ ቦምብ ጥቃቶች እና ግድያዎቹ እንደቀጠሉ በመሆኑ የሰላም ንግግር ጥረቶችን ይበልጡን እየተወሳሰበ መጥቷል

በግጭት እየታመሰች ባለችው በቡሩንዲ ሰላም ለማምጣት የክልሉ ሀገሮች አዲሱ ሸምጋይ እንዲሆኑ የቀድሞ የታንዛኒያ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓን መሰየማቸው የሰላም ሂደቱን ያንቀሳቅሰዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር ። ይሁን እንጂ ሰኞ ታንዜንያዋ አሩሻ ከተማ ሊካሄድ የነበረው እስከወሩ መጨረሻ ገደማ እንዲዘገይ ተደርጓል። በዚህ መሃልም በሀገሪቱ እስሩ፣ የእጅ ቦምብ ጥቃቶች እና ግድያዎቹ እንደቀጠሉ በመሆኑ የሰላም ንግግር ጥረቶችን ይበልጡን እየተወሳሰበ መጥቷል።

ሰኞ ሊጀመር ታቅዶ የነበረው የቡሩንዲ ፖለቲካ ሽምግልና ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ስለምን ባለስልጣናት ከመንግስቱና ከተቃዋሚዎቹ ጋራ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል።

ካሁን ቀደምም የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙስቬኒ የመሩት የሽምግልና ጥረት ውጤት እንዳላመጣ ይታወሳል።

የብሩንዲ ፖሊስ
የብሩንዲ ፖሊስ

ባለፈው መጋቢት ወር ታዲያ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ኢ ኤ ሲ የቀድሞውን የታንዜንያ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓን ድርድሩን እንዲመሩና ለአንድ ዓመት የዘለቀውን የፖሌቲካ ቀውስ መፍትሄ እንዲፈልጉ ሾመዋቸዋል። ለድርድሩ ቀረቤታ ያላቸው ባለስልጣናት እንዳሉት የሀገሪቱ መንግስት በመንግስትና በጸታት ባለልስጣናት ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው ብሎ ከሚወነጅላቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር መነጋጋር ላይ እያመነታ ነው።

የመንግስቱ ቃል አቀባይ ዊሊ ኒያማኢትዌ ድርድሮቹ ሰፋ ብለው በስደት ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖችንም ማሳተፍ ይገባቸዋል ብለዋል።

"በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ንግግሮች እየተካሄዱ ያሉት ቡሩንዲያውያን ዕርስ በርስ የሚያደርጉትን ውይይት እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም/ኮሚሽን ስላለን ነው። ወደ ሃገር መምጣት የማይችሉትን ቡሩንዲያውያን ያሉበት ቦታ እየደረስን ለማሳተፍ ስንልም ውይይቱን በውጭም ለማካሄድ ዝግጁ ነን።" ብለዋል።

አብዛኛው አባላቱ በውጭ በስደት ላይ ያሉ ቡሩንዲያውያን የሆነው ተቃዋሚ ቡድን (CORENABU)፣ መንግስት በፖለቲካ ድርድሩ እንዳንሳተፍ እየከላከለ ነው በማለት አማረዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አርማ
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አርማ

የኢምነስቲ ኢንተርናሲናል የክልሉ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሳራ ጃክሰን የድርድሩ መጓተት የሀገሪቱ መረጋጋት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ያስረዳሉ ።

"ድርድሮች በተደጋጋሚ እየዘገዩ መሆናቸውን እያየን ነው። በዚህ የሚጎዳው ተራው ቡሩንዲያዊ ነው። በኢኪኖሚው ሁኔታ፣ የተለያዩ ወገኖች ይበልጡን ጽንፍ እየያዙ በመምጣታቸው በታወቁ ሰዎች ላይ በሚደርሰው ግድያ የሚጎዳው ህዝቡ ነው።" ብለዋል።

ሁከቱና የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየተባባሰ መሆኑንም የአምነስቲዋ ሳራ ጃክሰን አክለዋል።

"ባለፈው ዓመት ግድያዎች፣ የማሰቃየት ተግባሮች፣ በዘፈቀደ ማሰር ተፈጽሟል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደግሞ ከሁሉም ወገኖች በሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዒላማ ያደረጉ ግድያዎች እና ጥቃቶች ተባብሰዋል።" ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት አንድ ከፍተኛ የቡሩንዲ ብርጋዴር ጄነራል ባለቤታቸውን ጠባቂያቸው በታጣቂ ጥይት ተገድለዋል። ድርጊቱን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፒየር ኑኩሪዚዛ አውግዘውታል።

በውጭ በስደት ላይ ያሉ ቡሩንዲያውያን የሆነው ተቃዋሚ ቡድን(CORENABU) የተባለው የፖለቲካ ንቅናቄ መሪ ዲዩዶኔ ቢራሂንዱካ ቡሩንዲ የአመራር ለውጥ ያስፈልጋታል ይላሉ።

"እነዚህ ሰዎች ሀገሪቱን ለመምራት ብቁ ናቸው ብለን አናምንም። እጆቻቸው ንጹህ አይደሉማ። አንዳንዶቹ እጃቸው ላይ ደም አለ። እንደኛ ዕምነት ከአዲሱ ትውልድ የወጡ ፖሌቲከኞች በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ርዳታ አመራሩን መያዝ አለባቸው።" ብለዋል።

ብቡሩንዲ ወደ ብጥብጥ እያሽቆለቆለች የሄደችው ፕሬዚደንቱ ፒየር ኑኩሩዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ካሉ በኋላ ነው። ነቃፊዎች ህገ መንግስቱን ጥሰዋል ቢሏቸውም ፕሬዚደንቱ በምርጫው አሸንፈው መንበረ ስልጣኑን ለሶስተኛ ጊዜ ያዙት ። በዚያ መካከል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተካሂዶባቸዋል። ሁከት የቀላቀሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችም ተደርገዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሰረት የቡሩንዲው ቀውስ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከአራት መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የሚበልጡ ዜጎቿ ሃገር ጥለው ተሰደዋል።

መሐመድ ዩሱፍ ከናይሮቢ ያጠናቀረው ዘገባ ነው፣ ቆንጂት ታዬ ነው ያቀረበችው።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG