ቡሩንዲ ውስጥ ለዘጠኝ ወራት ከዘለቀው የፖለቲካ ቀውስ ተያይዞ ስለሚደርሱ የከፉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች የሚወጡት ሪፖርቶች በጥልቅ ያሳሰቡት መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማርክ ቶነር ትናንት ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ የቡሩንዲ መንግሥት በቅርብ ጊዜያት ተፈጽመዋል የተባሉት ወንጀሎች በነጻ ኣካል ምርመራ እንዲካሄድ ባስቸኩዋይ ፈቃድ እንዲሰጥ እና ወንጀሉን የፈጸሙትንም በተጠያቂነት እንዲይዝ አሳስበዋል።
የቡሩንዲ የጸጥታ ሓይሎች ዜጎችን አሰቃይተዋል፣ ካለፍርድ ገድለዋል፡ ሴቶችን በርብርብ ደፍረዋል፣ የጅምላ መቃብሮችም ተገኝተዋል የሚሉ በርካታ ሪፖርቶች ወጥተዋል። በዚህም የተነሳ የተ.መ .ድ. የሰብዓዊ መብቶች ኮምሽነር ዜይድ ራኣድ አል ሁሴን "እነዚህ አሳሳቢ ሁኔታዎችና የቀውሱ ብሄረሰባዊ ገጽታ እየሰፋ መምጣቱ እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ እንዳለ ያመለክታል" በማለት ባለፈው ዓርብ መግለጫ አውጥተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አክለውም የቡሩንዲ መንግሥት ተፈጽመዋል የተባሉትን ወንጀሎች የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች ባስቸኳይ ያለምንም ዕንቅፋት ገብተው ምርመራ እንዲያካሂዱ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ብጥብጡን ለማስቆም አምስት ሺህ ወታደሮች እንላክ ብሎ ባለፈው ወር ቢጠይቅ የቡሩንዲ መንግሥት ዕምቢ ማለቱ እና ያለፈቃዴ ቢገቡ ጥቃት ይደርስባቸዋል ሲል ማስጠንቀቁ ይታወሳል። የዜና ዘገባችንን ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል ይጫኑ።