በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ጾታዊ ጥቃቱ ተባብሷል፤ አንዷ ተጠቂ ዜይነብ ትናገራለች


ወታደሩ ሴቶችን እያነጋገረ ካርቱም ሱዳን እአአ ሰኔ 6/2023
ወታደሩ ሴቶችን እያነጋገረ ካርቱም ሱዳን እአአ ሰኔ 6/2023

በጦርነት ከተበጠበጠችው የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም፣ ለቅቃ በመሸሽ ላይ የነበረችው ዜይነብ እንደምትናገረው፣ አንድ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባል ደረቷ ላይ መሣሪያ ደግኖባት ደፈራት፡፡

በእርሷ፣ በታናሽ እህቷ እና አብረዋቸው ይጓዙ በነበሩ ሁለት ሴቶች ላይ ስለተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት፣ ዜይነብ፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዝርዝር አውስታለች፡፡ አብራቸው የነበረችው አንደኛዪቱ ሴት፣ ሕፃን ልጅ ይዛ በመሰደድ ላይ እንደነበረች ዜይነብ ገልጻለች፡፡

እንደዜይነብ ሁሉ፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ፣ በገዛ መኖሪያ ቤታቸው፣ በየመንገዱ ወይም ታጣቂዎች በወረሯቸው ሆቴሎች ውስጥ፣ እንደተደፈሩ የተናገሩ ሴቶች ብዙዎች ናቸው፡፡

“ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከአንድ ወር በኋላ ካርቱምን ለቅቀን ወጣን፡፡ የተሳፈርንበትን ሚኒባስ፣ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎች፣ በዘረጉት የፍተሻ ኬላ ላይ አስቆሙት፡፡ ፍርሃት ዋጠን፡፡ ከመኪናው አስወረዱንና በእግራችን ወደ አንድ መጋዘን ይዘውን ሔዱ፡፡ ከዚያም የሲቪል ልብስ የለበሰ አዛዣቸው የሚመስል ሰው፣ መሬቱ ላይ በይ ተኚ፤ አለኝ፤” ብላለች ዜይነብ፡፡

አንደኛው፣ እንዳልንቀሳቀስ ከመሬቱ ጋራ አጣብቆ ሲይዝለት ሌላኛው ደፈረኝ፡፡ እርሱ ሲበቃው ደግሞ ተቀያየሩና ሌላው ደፈረኝ፡፡ እህቴን እዚያው ሊያስቀሯት ፈልገው ነበር፡፡ እግራቸው ላይ ወድቄ ለምኛቸው ነው የለቀቋት፤”

ዜይነብ ማስረዳቷን ቀጥላለች፤ “አንደኛው፣ እንዳልንቀሳቀስ ከመሬቱ ጋራ አጣብቆ ሲይዝለት ሌላኛው ደፈረኝ፡፡ እርሱ ሲበቃው ደግሞ ተቀያየሩና ሌላው ደፈረኝ፡፡ እህቴን እዚያው ሊያስቀሯት ፈልገው ነበር፡፡ እግራቸው ላይ ወድቄ ለምኛቸው ነው የለቀቋት፤” ብላለች፡፡

ዜይነብንና ሌሎቹን ሴቶች ከደፈሯቸው በኋላ፣ መንገዳቸውን እንዲቀጥሉ ፈቅደውላቸው፣ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ማዳኒ ከተማ ከገቡ በኋላ፣ የደረሰባቸውን ለፖሊስ አስታውቀው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ዜይነብ ተናግራለች፡፡

ዜይነብ፣ የተፈጸመባትን ወሲባዊ ጥቃት፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዝርዝር ያወሳችው፣ በስደት ከተጠለለችበት ሌላ ሀገር ኾና ነው፡፡ “ከእኛም በፊት ሴቶች ሲደፈሩ ነበር፤ በእኛም አይቆምም፣ ይቀጥላል፤” ብላለች፡፡

እ.አ.አ ሚያዝያ 15 ቀን በጀመረው የሱዳን ጦርነት፣ ቢያንስ 1ሺሕ800 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከ1ነጥብ5 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የጥቃት ሰለባዎች፣ የሕክምና ሠራተኞች እና ማኅበራዊ አንቂዎች፣ እየደረሰ ያለው ጾታዊ ጥቃት፥ ጦርነቱ በሕዝቡ ላይ የፈጠረውን ሽብር ምን ያህል ዕጥፍ ድርብ እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡

በደቡባዊ ካርቱም በአንድ መጋዘን ላይ የተነሳ እሳት ቃጠሎ ሰማዩን ሽፍኖት ይታያል፣ ካርቱም፤ ሱዳን
በደቡባዊ ካርቱም በአንድ መጋዘን ላይ የተነሳ እሳት ቃጠሎ ሰማዩን ሽፍኖት ይታያል፣ ካርቱም፤ ሱዳን

አብዛኞቹ ሰዎች የተናገሩት፣ በእነርሱ ወይም በሌሎች ላይ የበቀል ጥቃት እንዳይደርስ በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ በመጠየቅ ሲኾን፣ እንደ ዜይነብ ተለዋጭ ስም ሰጥተው የተናገሩም አሉ፡፡

የሱዳን የጦር ሠራዊት አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታሕ አል ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎች አዛዡ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ፣ እየተፈጸመ ስለሚገኘው ጥቃት፣ አንደኛው ሌላውን ይወነጅላሉ፡፡

የሰብአዊ መብቶች ጠበቃው ጄሃኒ ሄንሪ በበኩላቸው፣ “ከአሁን ቀደም፣ ሁለቱም ወገኖች፣ ዘግናኝ ወሲባዊ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፤” ብለዋል፡፡ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተከላካይ ቡድን የተባለው መንግሥታዊ ድርጅት ባቀረበው ሪፖርት፣ በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ፣ በ49 ሴቶች ላይ ጥቃት መድረሱን እንደመዘገበ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት፣ ኻርቱም ውስጥ፥ ምንም ጥቃት አይደርስብኝም፤ ብላ የማትሰጋ ሴት ማግኘት አይቻልም፡፡ በገዛ ቤታቸው እያሉም፣ ከአሁን አሁን መጡብን፤ ብለው ይፈራሉ፤”

የድርጅቱ ሓላፊ ሱላይማ ኢሻክ አል ካሊፋ፣ ከስድስቱ በስተቀር የተቀሩት ተጠቂዎች በሙሉ፣ “ጥቃቱን ያደረሱብን የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን መለዮ የለበሱ ወንዶች ናቸው፤” ማለታቸውን አመልክተዋል፡፡ በየቀኑ ዐዲስ ሪፖርቶች እንደሚደርሷቸውም ገልጸዋል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት፣ ኻርቱም ውስጥ፥ ምንም ጥቃት አይደርስብኝም፤ ብላ የማትሰጋ ሴት ማግኘት አይቻልም፡፡ በገዛ ቤታቸው እያሉም፣ ከአሁን አሁን መጡብን፤ ብለው ይፈራሉ፤” ብለዋል፡፡

በሱዳኑ ጦርነት፣ ከሁሉም የሚከፋው ውጊያ የተካሔደው፣ በዋና ከተማዋ ኻርቱም እና በዳርፉር ክፍለ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ ዳርፉር፣ የቀድሞው ዓምባገነን መሪ ኦመር ሐሰን አል በሺር፣ በጭካኔው በታወቀው ጃንጃዊድ ሚሊሺያ፣ ሕዝቡን ያስደበደቡበት አካባቢ ሲኾን፣ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉም፣ ከዚኹ ኃይል ውስጥ የወጣ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መሠረት፣ ጃንጃዊዶች፥ እ.አ.አ በ2003 በአካሔዱት የለየለት አረመኔያዊ የጥቃት ዘመቻ፣ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የዘር ማጥፋት፣ የጦርነት ወንጀል እና በሰብእና ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል፡፡

አሁን ደግሞ፣ ዳግም በጅምላ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶች እየተፈጸሙ እንዳሉ የሚገልጹ ሪፖርቶች እየቀረቡ መኾኑን፣ በሱዳን የተመድ የሴቶች ቢሮ ተወካይ አድጃራቱ ኢንዳዬ ተናግረዋል፡፡ አንዲት፣ የሱዳን የሴቶች መብት በተግባር ኮሚቴ የተባለ አካል ተመራማሪ እንዳሉት፣ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ተብለው በመዝገብ የተያዙት ሰለባዎች ቁጥር፣ በተጨባጭ ካለው የሰለባዎች ብዛት እጅግ በጣም ጥቂቱ ነው፡፡

የሕክምና ሠራተኞች እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ ሆስፒታሎች ስለ ተዘረፉ ወይም ስለ ወደሙ ብዙዎች የጥቃት ሰለባዎች፣ የሕክምና ርዳታ አያገኙም፡፡ በጸጥታ ኃይሎች የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን፣ ለረጅም ጊዜ ሲመዘግቡ የቆዩ አንድ ጠበቃ እንደተናገሩት፣ በሱዳን ውስጥ፣ ይህ ጥቃት ያልነካው አንድም የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ “አጥቂዎቹ ግድ የላቸውም፡፡ እንቡጥ ልጃገረዶችን ይደፍራሉ፡፡ ዕድሜአቸው የገፉ ሴቶችንም ይደፍራሉ፡፡ እናቶችን ከነልጆቻቸው ይደፍራሉ፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ፣ የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት እና አስቸኳይ የእርግዝና መከላከያ መድኃኒት ከባድ እጥረት እንዳለ ተገልጿል፡፡ የሱዳን የፋርማሲ ባለሞያዎች ማኅበር አባል፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት ቃል፣ ኹኔታው እጅግ አደገኛ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ማኅበራዊ አንቂዎች እና የሕክምና ርዳታ ሠራተኞች፣ እያንዳንዱን ጥቃት በሰነድ መዝግበው ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት፣ ጥቃቱን ያደረሱ ሰዎች ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

ካርቱምን ለቅቃ ስትሰደድ፣ በፍተሻ ኬላ ላይ፣ ከታናሽ እህቷ እና ከሌሎች ሴቶች ጋራ በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች አባላት የተደፈረችው ዜይነብ፣ ደፋሪዎቹ፣ አንድ ቀን ፍርዳቸውን አንድ ቀን ያገኛሉ፤ ብላ እንደምትጠብቅ ነገር ግን፣ ይህ ፍርድ ይፈጸማል የሚል እምነት እንደሌላት ገልጻለች፡፡

“እኔ ስለተፈጸመብኝ ጥቃት የምናገረው፣ በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ብዬ ነው፡፡ መንገዱ አደገኛ እንደኾነ እንዲያውቁትም ለማስጠንቀቅ በማለት ነው፡፡ ይኹንና፣ ለፖሊስ ሪፖርት ባደርግም፣ አንዳችም ርምጃ እንደማይወሰድ አውቄዋለኹ፡፡ ሰዎቹን ፈጽሞ አያገኟቸውም፤” ትላለች በቀቢጸ ተስፋ የተዋጠችው ዜይነብ፡፡

XS
SM
MD
LG