በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ዳግም የተኩስ አቁም ንግግር ጀምረዋል


በካርቱም ከታማ የቃጠሎ ጭስ ይታያል፡፡ ካርቱም፤ ሱዳን
በካርቱም ከታማ የቃጠሎ ጭስ ይታያል፡፡ ካርቱም፤ ሱዳን

የሱዳን ተፋላሚ ወታደራዊ ኃይሎች፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት፣ ዳግም የተኩስ አቁም ውይይት መጀመራቸውን፣ አል አረቢያ የተሰኘው የቴሌቭዥን ጣቢያ ዘግቧል፡፡

ኾኖም ተፃራሪዎቹ ኃይሎች፣ በመዲናዋ ካርቱም፣ በአየር እና በምድር የሚያደርጉትን ፍልሚያ ቀጥለዋል።

በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሚደረገው ውጊያ፣ ሲቪሎች መሠረታዊ አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል፤ ሕገ ወጥነት እንዲበራከትም በር ከፍቷል፤ ተብሏል።

በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ሰብአዊ ሥራዎችን ለማከናወን፣ ባለፈው ሳምንት መደረግ የነበረበት የተኩስ አቁም ሳይከበር ለበርካታ ጊዜያት ተጥሷል።

በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ባለቤትነት የተያዘው አል አረቢያ ቴሌቭዥን፣ ሁለቱ ወገኖች፣ በሦስተኛ ወገን ለመነጋጋር መስማማታቸውን ቢገልጽም፣ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጠም። ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም፣ እስከ አሁን በጉዳዩ ላይ የተናገሩት ነገር የለም፡፡

የሠራዊቱ አዛዥ አብዱል ፋታሕ አል ቡርሃን፣ ከሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሳል ቢን ፋርሃን ጋራ መነጋገራቸውን፣ የሱዳን ሉዓላዊ ም/ቤት አስታውቋል።

የጀዳው ንግግር ውጤታማ እንዲኾን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፥ ከሆስፒታሎች፣ ከሕዝብ መገልገያዎች፣ እንዲሁም ከመኖሪያ ቤቶች ለቆ እንዲወጣ፣ ቡርሃን አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን፣ የምክር ቤቱ መግለጫ ጨምሮ አስታውቋል።

የፈጥኖ ደራሹ አዛዥ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ደጋሎም በበኩላቸው፣ ከሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሳል ቢን ፋርሃን ጋራ መነጋገራቸውን፣ ባለፈው እሑድ ያስታወቁ ሲኾን፣ በጀዳ የሚካሔደውን ውይይት እንደሚደግፉ ተናግረው ነበር።

ሁለቱም ወታደራዊ መሪዎች፣ ዳግም በሁለቱ ሀገራት አደራዳሪነት ስለሚጀምረው የተኩስ ማቆም ውይይት ያሉት የለም።

XS
SM
MD
LG