የሱዳን ተፋላሚዎች በዩናይትድ ስቴትስ እና በሳዑዲ አረቢያ ሸምጋይነት የተስማሙበትን ተኩስ አቁም ካከበሩ በሁለቱ ወገኖች መካከል ንግግር ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዛሬ ሐሙስ በሰጡት ቃል “ሁለቱ ኃይሎች ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ከልባቸው ተገዢ መሆናቸውን በድርጊታቸው ግልጽ ካደረጉ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሳዑዲ አረብያ፣ ለግጭቱ ከድርድር የመነጨ መፍትሄ እንዲገኝ፣ ሁኔታዎችን እንደገና ለማመቻቸት ዝግጁ ናቸው” ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ መግለጫውን ያወጣችው፣ የሱዳን የጦር ሠራዊት፣ “የሰላም ስምምነቱን በተደጋጋሚ ጥሷል” በሚል፣ ከከሰሰው ከተፋላሚው የፈጥኖ ደራሽ ጦር ጋር የሚያደርገውን ንግግር ማቋረጡን ባስታወቀ ማግሥት ነው፡፡
ሁለቱ ወገኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን ለመፍቀድ እ አ አ ግንቦት 20 ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርመዋል፡፡ ከዚያም በኋላ እ ኤ አ ግንቦት 29 ለተጨማሪ አምስት ቀናት ለማራዘም ተስማምተዋል፡፡
የተኩስ አቁሙን አፈጻጸም የሚከታተሉት ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረብያ ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን መጣሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ጥያቄ፣ ትናንት ረቡዕ በሱዳን ጉዳይ 90 ደቂቃ የፈጀ ዝግ ስብሰባ አድርጓል፡፡
ዋና ጸሐፊው በአምስት ዓመቱ የሥራ ዘመናቸው ካሁን ቀደም እንዲህ ያለውን ስብሰባ የጠየቁት አራት ጊዜ ብቻ ሲሆን ቃል አቀባያቸው ስቲፈን ዱጃሪክ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በሱዳን በፖለቲካውም በሰብዐዊ ደህንነትም ከባድ ችግር ተደቅኖብናል፡፡ ዋና ጸሐፊው አንዳንድ ሀሳቦችን ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት ማጋራት ይፈልጋሉ” ብለዋል፡፡
የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የጦር ሠራዊቱ አዛዥ የጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኅይሉ መሪ ጄኔራል መሐመድ ሀምዳን ደጋሎን ጸብ ተከትሎ እ ኤ አ ሚያዝያ 15 በተቀሰቀሰው ከባድ ጦርነት በመታመስ ላይ ናት፡፡