ትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተው ረሃብ “ለፖለቲካ ዓላማ እየዋለ ነው” ሲል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ወቀሳ አሰምቷል።
"ክልሉ ውስጥ የተከሰተው ረሃብ የ1977ቱ ጋር ይተካከላል በሚል የተሠራጨው መረጃ ፍፁም የተሳሳተ ነው" ሲሉ የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ አስተባብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ደግሞ “ለረሃብ አደጋ የተጋለጡ ሚልዮኖችን ለመታደግ የቀረበው ጥሪ ፖለቲካዊ መባል የለበትም” ብለዋል።
“ከ1977 ዓ.ም. ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ የከፋ ድርቅ መከሰቱን” የሚያትተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዓርብ፣ ታኅሣስ 19/2016 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ “አሁን የተከሰተው ድርቅና ትግራይ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት ተደማምረው ከፍተኛ አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችሉ” አሳስቧል።
ፌዴራል መንግሥትና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ “ትግራይ ላይ እያንዣበበ ያለውን ረሃብና ሞት ለመታደግ ሕጋዊና ሞራላዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲል ጠይቋል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ “መንግሥት መላ አገሪቱ ውስጥ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ለማገዝ እየሠራ ነው” ብለዋል። አሁን ወደ አራት ሚሊየን የሚጠጋ ሰው በተለያዩ ክልሎች የድርቅ አደጋ እየተጋፈጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ትግራይ ላይ የተከሰተውን ድርቅ ከ1977ቱ ድርቅ ጋር ተመሣስሎ የተሰጠው መግለጫ “የተሳሳተ ነው፤ ይህንን ድርቅ ለፖለቲካ ጉዳይ ማዋል አይገባም” ብለዋል።
መንግሥት ወደ ክልሉ በቂ እርዳታ እየላከ ነው ያሉት ዶ/ር ለገሠ የክልሉ መሪዎች ካለፈው ወር ጀምሮ እያካሄዱት ያለውን ስብሰባ ተችተዋል።
በዶ/ር ለገሠ ወቀሳና ትችቶች ላይ የትግራይ ክልል አመራር አባላት አስተያየትን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ “ክልሉ ውስጥ ለመቁጠር የሚያዳግት ህይወት እያለፈ ነው” ብለዋል።
እርዳታ ሰጭ ተቋማትና ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሰነዱት የድርቅና የረሃብ አደጋ ፖለቲካዊ ነው የሚያስብል አይደለም፤ ክልሉ ውስጥ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ተከትሎ ሚልዮኖችን ለማዳን የቀረበ ጥሪ ነው”
“እርዳታ ሰጭ ተቋማትና ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሰነዱት የድርቅና የረሃብ አደጋ ፖለቲካዊ ነው የሚያስብል አይደለም፤ ክልሉ ውስጥ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ተከትሎ ሚልዮኖችን ለማዳን የቀረበ ጥሪ ነው” ብለዋል።
በሰውና በእንስሳት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው "ይህንን ለመከላከልም ፌደራሉ መንግሥትና ዓለምአቀፍ ረጂ አካላት ተባብረው ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።
ክልሉ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመንግሥታቸው ትዕዛዝ እንዲሰጡና አጋዥ ተቋማትም እንዲያግዙ አቶ ጌታቸው ተማፅነዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም “በአሁኑ ጊዜ በረሃብ ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉን አላረጋገጥንም” ብለው ነበር።
መድረክ / ፎረም