በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልልን የከበደ ረሃብ ያሰጋዋል - ተመድ


በጦርነት በተጎዳው የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የከበደ ረሃብ አደጋን ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ አንድ የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የድርጅቱን የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸኃፊ እና የአጣዳፊ እርዳታ አስተባባሪው ማርክ ሎውኮክ "የሚሰጠው እርዳታ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከፍ ካልተደረገ ከባድ የረሃብ አደጋ ይደቀናል" ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አገኘሁት ያለውን የገለጻቸውን ይዘት ጠቅሶ ዘግቧል።

የትጥቅ ግጭት፣ የሁከት እና የምግብ ዋስትና ዕጥረት አዙሪቱን ለመስበር በአስቸኳይ ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፣ የጸጥታ ምክር ቤቱ ማንኛውንም እርምጃ ወስዶ የከበደ ረሃብ ቸነፈር ይከላከል ሲሉ ያሳሰቡት ባለሥልጣኑ ከክልሉ ህዝብ ሃያ ከመቶው አጣዳፊ የምግብ ዋስትና ዕጦት የተደቀነበት መሆኑን እና አሁንም በትግራይ የሚደርሰው ውድመት እና በሲቪሎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል ማለታቸውን ኤኤፍፒ አመልክቷል።

የትግራይ ክልል ግጭት ከተጀመረ ወዲህ ባለፈው የስድስት ወር ተኩል ጊዜ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ሲቪሎች እየተገደሉ እና እየቆሰሉ ናቸው፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌላም ዘግናኝ ወሲባዊ ጥቃት በተቀነባበረ መንገድ ተስፋፍቷል ማለታቸውን የዜና አውታሩ ተመልክቸዋለሁ ያለውን የባለሥልጣኑን ማስታወሻ ጠቅሶ ዘግቧል።

በክልሉ ዘጠና ከመቶ የሚሆነው የእርሻ ሰብል በዝርፊያ ወይም በቃጠሎ ወድሟል። ሰማኒያ ከመቶው የቀንድ ከብት ተዘርፏል ወይም ታርዷል ማለታቸውንም አክሏል።

የተመዱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊው በማያያዝ ከለፈው መጋቢት ወር ወዲህ መሻሻል የታየ ቢሆንም እና በክልሉ በአካባቢ ባለሥልጣናት ደረጃ ትብብር እየተደረገ ቢሆም ባጠቃላዩ በቅርብ ጊዜያት የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነት ሁኔታው አሽቆልቁሏል፣ ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ነፍስ አድን እርዳታ ለማድረስ በሚደረጉ የሰብዓዊ ረድኤት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቃት የማደናቀፍ ወይም የማዘግየት አድራጎት እየተፈጸመ ነው። ባለፈው የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ስምንት የእርዳታ ሰራተኞች ተገድለዋል በማለት የጸጥታ ምክር ቤቱን ማሳሰባቸውን ዘገባው አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ጠይቀን እናቀርባለን።

XS
SM
MD
LG