በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ሰዎች በረሃብ ሲሰደዱ ህፃናት ተትተዋል


ፎቶ ፋይል፦ ሰቆጣ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ ሰቆጣ ከተማ

ጦርነት ወደ ደቆሳት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰነው ክፍሏ ወደ ከፍተኛ ረሃብ እየገባች ነው ወደሚላት የትግራይ ክልል፣ በወራት ጊዜ ውስጥ የገባው እርዳታ፣ ጥቂት እና አዝጋሚ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እጅግ በጠናው ረሃብ ሳቢያ ለመሰደድ ከተገደዱ የትግራይ ተወላጆች ውስጥ፣ አንዳንዶቹ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለመሄድ እስከመገድድ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡

ሰቆጣ ጦርነትና ረሀብን በመሸሽ ከትግራይ የተፈናቀሉ የብዙ ሺሕ ሰዎች መኖሪያ ናት፡፡ ሁል ጊዜ ጧት ጧት በከተማው ወደሚገኙ መንግሥታዊ ወዳልሆኑ የእርዳታ መስጫ ጣቢያዎች፣ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ይሰባሰባሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ የሚሰጣቸው ምግብ ይኖራል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን አይኖርም፡፡ 10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ትግራይ ለዓመት ያህል ለሰብአዊ እርዳታ ዝግ ሆና ትገኛለች፡፡ ወደ ክልሉ ስላልደረሰው እርዳታ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ አማጽያን እርስ በእርሳቸው ይወነጃጀላሉ፡፡

“ቢያንስ 1ሺ 900 ህጻናት ከወዲሁ በረሃብ ሞተዋል” የሚሉት የረድኤት ድርጅቶችና የክልሉ ጤና ባለሥልጣናት፣ ትግራይ ውስጥ ወደ 700ሺ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ከፍተኛ ረሃብ በተጠጋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡

ካሳሁን ባዬ የስድስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ቤተሰባቸውን ትተው ሰሞኑን ከትግራይ ሰቆጣ ገብተዋል፡፡ ነፍሰጡር የነበረችው ባለቤታቸው ወልዳ እዚያው መቅረቷን ይናገራሉ። "እዚያ የምበላው የለኝም። ወልዳለች እሷ እዚያው አትቀርም።" ይላሉ። ምግብ ወዳለበት ቦታ ካልመጡ ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው። "ምን ያደርጋል በክፋት ነው የመጣው እንጂ ሌላ ምንም የለም" ስሉም ሁኔታውን ያማርራሉ።

እሳቸው የሚሉት፣ የቤተሰባቸው አባላት የሚበላ ምንም ነገር የሌላቸው መሆኑን ያውቃሉ፣ ግን ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እሳቸው ወደዚያው እስኪመለሱ ድረስ በህይወት ከቆዩዋቸው፣ ወደ ሰቆጣ ሊያመጧቸው ይሞክራሉ፡፡ እነሱን ወደኋላ መተዋቸው በመጨከን አይደለም ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታው እሳቸው ሊሸከሙት ከሚችሉ በላይ ነው፡፡

መንግሥት ጋዜጠኞችን ወደ ትግራይ እንዳይገቡ በማገዱና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትንም ዝግ እንዲሆን በማድረጉ፣ ስለቀውሱ የተሟላ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ቪኦኤ ሰሞኑን ወደ ሰቆጣ በመሄድ በዚያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለማነጋገር ችሏል፡፡

ካሳ ተጋሩ የአማራ ብሄር ተወላጅ ናቸው፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ባለቤታቸው ከሳቸውና ከልጆቻቸው ጋር አብረዋቸው አለመምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለ ልጃቸው ሲናገሩም "እዛ ድንበር ስለሆን አማርኛ ቋንቋ እራሱ አትችልም። ትግርኛ ነው የምትናገረው። እና ሁል ጊዜ እንደው መቼ ነው ሰላም የሚሆነው? እና አባቴን አገኘው ይሆን ትላለች።" ይላሉ።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች የአማራ ክልልን ጨምሮ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደረገው ብሄር ተኮር ግድያ መኖሩን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡ “ሰዎች ከትግራይ አምልጠው የሚወጡበትን የሰብአዊነት ኮሪደር መፍጠሩ ቀውሱን በማርገብ ይረዳል” ይላሉ፡፡

ሳራ ዲርዶርፍ ሚለር መሰረቱን ዋሽንግተን ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነው የሪፊጂ ኢንተርናሽናል ድርጅት ፌሎ ናቸው፡፡

“በትክክል፤ ከዚያ ለቀው መውጣት የሚፈልጉ ሰላማዊ ሰዎች የሚወጡባቸው ተጨማሪ መንገዶች ያስፈላጋቸዋል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሃ ነው። እጅግ መሰረታዊ የሆነ የስደተኝነት ሀሁ ነው፡፡” ብለዋል።

በሰቆጣ የእርዳታ ሠራተኛዋ ዝናሽ ወርቁ ሁሉም ሰው ዕርዳታ ማግኘት አለበት ትላለች።

"ተፈናቅሎ ከየትም ይምጣ ከየትም። ሰው በሰውነቱ ደረጃ ማግኘት ያለበትን ድጋፍ ማግኘት አለበት። በቃ ይሄ ነው የሰው መገለጫው። ስንፈጠር ጀምሮ ወደዚህ የመጣንበት አላማ ይህ ነው። ስለዚህ ነገ የተወሰኑ ባለሥልጣኖች ወይም ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ባለመስማማታቸው የሰው ሕይወት ማለፍ የለበትም።" ብለዋል።

በሌላም በኩል ተስፋ መቁረጥ አሁንም ሰዎችን ወደ ሰቆጣ ተፈናቅለው እንዲመጡ እያደረጋቸው ነው፡፡ ከነዚህ አንዱ የሆኑት ቀናው አስፋው ናቸው።

"ዝም ብዬ መንገድ መንገዱን እየዋልኩ እያደርኩኝ አራት ቀንና አራት ለሌት ስጓዝ ነው የመጣሁት በረሃብና በጥም። ረሃብ ያስፈራል። እሞታለሁ ብዬ እያወኩ ነው የመጣሁት። መንገድ ለመንገድ እየሄድኩ ልሙት ብዬ እርግጥ መጥቻለሁ። ሰራዊቱም አልጠየቀኝም ዝም ብለው ሰደዱኝ" ብለዋል።

ብዙዎቹ ሰዎች ትግራይን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ትግራይ ውስጥ አዋቂና ህጻናት ሰዎች በረሃብ ሲሞቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

/የቪኦኤ ዘጋቢ ሄንሪ ዊልክንስ ያጠናቀረው ዘገባ ነው/

በትግራይ ሰዎች በረሃብ ሲሰደዱ ህፃናት ተትተዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:29 0:00

XS
SM
MD
LG