በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ረሃብ 'በከፍተኛ መጠን' መጨመሩን ተመድ አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ ርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ሲጓዝ
ፎቶ ፋይል፦ ርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ሲጓዝ

በጦርነት በተጎዳው የትግራይ ክልል ለከፋ የምግብ እጥረት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እና፣ በቅርቡ የምግብ ርዳታ መቆሙን ተከትሎ፣ ሁኔታዎች እየተባባሱ ሊሄዱ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ፤ሰኞ ዕለት ይፋ ባደረገው ወቅታዊ ሪፖርት፣ በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨማሪ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖሩ 8.8 ሚሊየን ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት በኅዳር ወር ከተፈረመ ወዲህ ወደ ክልሉ የሚገባው የርዳታ መጠን ቀስ በቀስ እንዲጨምር አስችሎ የነበረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ ምግብ እጥረት ምክንያት ለውስብስብ የጤና ችግር የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨምረ መሆኑን ክልሉ ይፋ አድርጓል።

ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር፣ በትግራይ፣ በከፍተኛ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በ196 ከመቶ ጨምሯል"

"ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር፣ በትግራይ፣ በከፍተኛ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በ196 ከመቶ ጨምሯል" ያለው የኦቻ ሪፖርት፣ የአሃዙ መጨመር "በከፊል የተሻለ የጤና ተቋማት ተደራሽነት እና የመረጃ አሰባሰብ" በመኖሩ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።

"ለትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረው የምግብ እርዳታ ለተረጂዎቹ እንደማይደርስ ገልፀው ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እርዳታ ማቋረጣቸውን ተከትሎ፣ በትግራይ ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የምግብ ዋስትና እጦት እየተባባሰ ሄዷል" ብሏል ኦቻ በሪፖርቱ።

በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ሚያዚያ ወር ከነበረው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፣ በመላ ሀገሪቱ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት ወደ ህክምና ተቋማት የሚገቡ ሰዎች ቁጥርም በ15 ከመቶ መጨመሩን ኦቻ በሪፖርቱ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG