በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ተቃዋሚዎች በረሃብ ምላሽ ጉዳይ ባለሥልጣናቱን ወቀሱ


የትግራይ ተቃዋሚዎች በረሃብ ምላሽ ጉዳይ ባለሥልጣናቱን ወቀሱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:18 0:00

የትግራይ ተቃዋሚዎች በረሃብ ምላሽ ጉዳይ ባለሥልጣናቱን ወቀሱ

“የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ከአንድ ወር በላይ በስብሰባ ተጠምደዋል” ሲሉ አራት የክልል ፓርቲዎች ወቀሳ አሰምተዋል።

ዓረና ትግራይ፣ ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ውድብ ናፅነት የሚባሉ የክልሉ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በተራዘመ ስብሰባቸው ምክንያት ባለሥልጣናቱ ለረሃቡ ምላሽ ካለመስጠታቸው በተጨማሪ መንግሥታዊ አገልግሎቶችም መስተጓጎላቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር፤ ዶ/ር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር ለቪኦኤ በሰጡት ምላሽ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ኮሚቴ አዋቅሮ ለረሃቡ አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ነው” ብለዋል።

ትግራይ ውስጥ በረሃብ ምክንያት ሰው እየሞተ መሆኑን “ኪዳን ለሥር ነቀል ለውጥ” በሚል የጋራ ጥላ ሥር በተደራጁት አራቱ ፓርቲዎች ዓረና ትግራይ፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና ውድብ ናፅነት ተናግረዋል።

ረሃቡን ዓለም እንዲያውቀውና ትኩረት እንዲያገኝ አለመደረጉን የዓረና ለዴሞክራሲ እና ሉአላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ አመልክተው ለጋሾች ዘንድ ‘ወደ ክልሉ የሚላክ እርዳታ ይዘረፋል’ የሚል ሥጋት መኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ገልፀዋል።

ክልሉ ውስጥ ያለው ረሃብ እንዳይታወቅ እየተሸፈነ ነው”

“ክልሉ ውስጥ ያለው ረሃብ እንዳይታወቅ እየተሸፈነ ነው” ሲሉ ክሥ ያሰሙት አቶ ዓምዶም “መሪዎቹ የህዝቡን መራብ ችላ ብለው ከአንድ ወር በላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።

“የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር፣ የፀጥታ አመራር አባላት፣ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የቀድሞ የህወሃት መሪዎች ድርቁንና ረሃቡን ችላ ብለው ከ35 ቀናት በላይ ለግል ጉዳያቸው፣ ለሥልጣንና ለጥቅም ትኩረት ሰጥተው ስብሰባ ላይ ናቸው። የዘንድሮው ድርቅ የከፋው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ችላ ስላሉት ነው። በዚህም ህዝባችን ተበትኖ በረሃብ እየሞተ ነው። ይህ መቆም አለበት።” ብለዋል አቶ ዓምዶም።

የክልሉን ውስጣዊ አቅም በመጠቀም፣ እንዲሁም ባለሃብቶችና ተቋማትን በማስተባበር ለረሃቡ መፍትኄ ማግኘት እንደሚቻል የአረናው መሪ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ከወር በላይ በተራዘመው የክልሉ መሪዎች ስብሰባ ለመንግሥታዊ አገልግሎትም መስተጓጎል ሰበብ መሆኑን የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ኃይሉ ጠቁመው “ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ስብሰባ ተብሎ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ዞኖች ስብሰባ ላይ ናቸው። ህዝባችን ትንሽም ቢሆን አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። መታወቂያ ለማግኘት እንኳን ተቸግሯል። አስተዳድራለሁ ብሎ ቢሮዎች የያዘ አካል ተቋማቱን ዘግቶ ከሰላሣ በላይ ቀናት ስብሰባ ላይ ነኝ እያለ ነው” ብለዋል።

የህወሃት መሪዎችና የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ካለፈው ወር አንስቶ ስብሰባ ላይ ሲሆኑ እየተወያዩባቸው ስላሉ ጉዳዮች ግን በይፋ የሰጡት መረጃ የለም።

ከፓርቲዎቹ በተሰሙ ክሦች ላይ መልስ እንዲሰጡ የጠየቅናቸው “የተራዘመ” የተባለው ስብሰባ ተሣታፊ የትግራይ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶ/ር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር ‘ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለረሃቡ ትኩረት አልሰጠም’ ተብሎ የቀረበውን ክሥ እንደማይቀበሉ አመልክተው “አጣዳፊ ምላሽ ለመስጠት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጭምር የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

“የክልሉ መሪዎች መንግሥታዊ ሥራን ወደ ጎን ትተው በስብሰባ ተጠምደዋል” ተብሎ ስለተነሣው ወቀሳ ግን ጥያቄው እርሣቸውን እንደማይመለከትና ስብሰባውን የጠሩት አካላት ሊመልሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

የትግራይ ተቃዋሚዎች በረሃብ ምላሽ ጉዳይ ባለሥልጣናቱን ወቀሱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:17 0:00

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG