በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትግራይ ውስጥ ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ በላይ ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተዘገበ


ፎቶ ፋይል፦ የእርዳታ እህል በትግራይ መረዳጃ ማህበር ለነዋሪዎች ሲከፋፈል በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል አጉላ ከተማ እአአ ግንቦት 8/2021
ፎቶ ፋይል፦ የእርዳታ እህል በትግራይ መረዳጃ ማህበር ለነዋሪዎች ሲከፋፈል በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል አጉላ ከተማ እአአ ግንቦት 8/2021

በትግራይ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ግጭት ካበቃበት ካለፈው የጥቅምት ወር አንስቶ ‘ቁጥራቸው 1,329 የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን አረጋግጠናል’ ሲሉ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች አስታወቁ።

የአካባቢ የጤና ባለስልጣናት እና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ባካሄዱት በዚህ ጥናት፡ ረሃብ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ዋነኛው የሞት መንስኤ ሆኗል ብለዋል። ጥናት ከተደረገባቸው ውስጥ ከ68 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች በረሃብ ሳቢያ ማለፋቸውንም አመልክተዋል።

ጥናቱ የጤና ባለሙያዎች ከነሀሴ 9 እስከ ነሃሴ 23 ዓም ትግራይ ውስጥ ባሉ ዘጠኝ ወረዳዎች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው 53 የመጠለያ ካምፖች ቤት-ለቤት በመሄድ ያካሄዱት መሆኑም ተገልጿል።

ትግራይ በአጠቃላይ 88 ወረዳዎች ሲኖሯት፤ በክልሉ የሚገኙት የተፈናቃይ መጠለያ ካምፖች ቁጥር ደግሞ 643 ነው። ጥናቱ የተካሄደው ከዚህ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ባለው ሕዝብ ላይ በመሆኑ በክልሉ በረሃብ ሳቢያ ለሞት የተዳረገው ሕዝብ ቁጥር ከዚህም የላቀ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ለረሃቡ መጥናት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፡ በክልሉ ለሰብአዊ ረድኤት በሚላክ የምግብ ዕርዳታ ላይ የሚፈጸመው ግዙፍ የተቀነባበረ ዘረፋ ባለፈው የመጋቢት ወር ከተደረሰበት በኋላ፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሰጡትን የምግብ እርዳታ ማቋረጣቸውን የተከለ ነው። የዕርዳታ እህል ስርቆቱ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም እየተፈጸመ መሆኑ መታወቁን ተከትሎም የምግብ ዕደላው ካለፈው የሰኔ ወር አንስቶ በብሔራዊ ደረጃ እንዲቋረጥ መደረጉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እገዳው እንዲነሳ የሚሻ ቢሆንም፤ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩላቸው መንግስት ከምግብ ዕርዳታ አሰጣጥ ስርዓት ተቆጣጣሪነቱ ውጭ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የክልሉ አጥኒዎች ጥናት አድርገው በመዘገቧቸው በሁሉም ዓይነት መንስኤዎች ለሕልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከእርዳታው መቋረጥ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገልጧል። በመጋቢት ወር 159 የነበረው የሟቾች ቁጥር በሃምሌ ወር በእጥፍ ከፍ ብሎ 305 መድረሱ ተዘግቧል።

አጠቃላይ ቁጥሩ 6 ሚሊዮን እንደሚደርስ ከሚገመተው የትግራይ ህዝብ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ ሲሆን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃም ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG