በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከትግራይ ክልል ህዝብ 'ግማሹ' የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከባድ መኪና ኮንቮይ ወደ ትግራይ እርዳታ በመጓዝ ላይ በኢሬብቲ መንደር፣ ኢትዮጵያ፤ እአአ 6/9/2022
ፎቶ ፋይል፦ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከባድ መኪና ኮንቮይ ወደ ትግራይ እርዳታ በመጓዝ ላይ በኢሬብቲ መንደር፣ ኢትዮጵያ፤ እአአ 6/9/2022

ከአጠቃላይ የትግራይ ክልል ሕዝብ ግማሽ የሚጠጋው በቂ ምግብ እንደማያገኝ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ። ሮይተርስ የድርጅቱን መግለጫ ጠቅሶ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ፤ እጥረቱ የተባባሰው ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በተካሄደው ጦርነት እና ግጭት ምክኒያት የእርዳታ ተቋማት ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎችን መድረስ በነዳጅ እጥረት ምክንያት መድረስ ባለመቻላቸው እንደሆነ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው መጋቢት ወር ለሰብዓዊነት በሚል ተኩስ አቁም በተናጠል ማወጁን ተከትሎ ዕርዳታ የማድረሱ ሂደት ቢቀጥልም፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እና እየከፋም እንደሚሄድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምገማ አመልክቷል።

"ረሃብ ስር ሰዷል፣ በምግብ እጥረት የሚጎዱ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል" ያለው የድርጅቱ ሪፖርት የዚህ ዐመት ምርት በጥቅምት ወር መሰብሰብ እስኪችል ድረስ ረሃቡ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን እና የከፋው ሁኔታ ገና ወደፊት እንደሚታይ ጨምሮ ገልጿል።

በትግራይ ክልል ከሚያጠቡ እናቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እንዲሁም ከአምስት ዐመት በታች ከሆኑ ህፃናት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በምግብ ዕጥረት መጠቃታቸውን እና እናቶችንም ለሞት እየዳረገ መሆኑን ሪፖርቱ ጨምሮ ጠቅሷል።

በመላዋ ትግራይ እና ጦርነቱ በጎዳቸው በአጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች 13 ሚሊየን ህዝብ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ይተገለፀ ሲሆን ይህ ቁጥር የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ጥር ወር ካወጣው ሪፖርት በ44 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ሮይተርስ በቂ ነዳጅ በማድረስ ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ምላሽ ለማግኘት ሞክሮ እንዳልተሳካለት ጠቅሶ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግሥት እና ትግራይ ክልልን በሚቆጣጠረው ህወሓት መካከል ይደረጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች መወነጃጀላቸውን በመቀጠላቸው እየደበዘዘ መሄዱንም አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG