በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ አስገድዶ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ


ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት) የተማረከና በአፋር ክልል ዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ተቀምጦ
ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት) የተማረከና በአፋር ክልል ዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ተቀምጦ

በጦርነት በደቀቀችው ትግራይ ክልል ያሉ ባለሥልጣናት ወጣቶች ከማዕከላዊ መንግስት ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት አንዲሳተፉ ለማስገደድ ቤተሰቦቻቸውን እያስፈራሩና እያሰሩ እንደሚገኙ ተይዘው የነበሩ ተዋጊዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረው ጦርነት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ አፈናቅሏል። ጦርነቱ ረሃብ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመትን ቢያስከትልም በሌሎች የዓለም ክፍሎች እየተካሄዱ ካሉ ጦርነቶች አንፃር ሲታይ በተለይም በዩክሬን እየተካሄደ ካለው አንፃር ዝቅተኛ ትኩረት እንደተሰጠው የሮይተርስ ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሃት) 6 ሚሊዮን የሚጠጉትን የክልሉ ነዋሪዎች ከማዕክላዊ መንግሥት ጭቆና ለመከላከል ትግል እያደረገ መሆኑን ሲገልጽ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ህወሃት በማዕከላዊ መንግሥት ላይ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር እስከ 2018 ድረሰ ይዞት የበረውን የበላይነት ለማስመለስ አመጽ ጀምሯል ሲሉ ይከሳሉ።

በክልሉ ከአካባቢዎች ነዋሪዎች፣ ተይዘው ከነበሩ ተዋጊዎች እንዲሁም ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከየካቲት እስከ ግንቦት በደርዘን የሚቆጠሩ ቃለ መጠይቆችን ማድረጉን በዘገባው ላይ ያሰፈረው ሮይተርስ አስገድዶ ምልመላውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ማግኘቱን ዘግቧል።

የትግራይ የውጪ ግንኙነት ቢሮን በመወከል ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ለሮይተርስ በላኩት ኢሜይል እንዳሉት ደግሞ በታችኛው እርከን የሚገኙ አንዳንድ ባለስልጣናት ስዎችን ለጦርነት ለመመልመልና ለመመዝገብ ዘመዶቻቸውን አስረው እንደነበር ጠቅሰው ይህ ግን አልፎ አልፎ የሚከሰት ድርጊት ነው ብለዋል። ታጋቾቹም እንደተለቀቁና አሳሪዎቹ ባለስልጣናትም እንደተቀጡ አክለዋል።

እስሩ የትግራይ መንግሥት ፖሊሲ አይደለም ሲሉ አክለዋል።

“በግዳጅ ምልመላ አለ የሚለው ክስ ትክክል አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ አግባብ ያልሆኑ አካሄዶች በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላይ ታይቷል። እነዚህ ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ እንጂ ሆን ተብለው የተደረጉ አይደሉም።” ብልዋል ፕ/ር ክንድያ።

ከፖሊስና ከአካባቢው ባለስልጣናት በህወሃት በኩል መልስ ለማግኘት ሮይተርስ ቢሞክርም መልስ ማግኘት አለመቻሉን ጠቅሷል። አብዛኞቹ የግንኙነት መስመሮች ከሰኔ ወር ጀምሮ እንደተቋረጡና አንዳንዶቹም ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ተቋርጠው እንደቀሩ ሪፖርቱ አክሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የግዳጅ ምልመላ መኖሩን የሚያመላክቱ በርካታ ሪፖርቶች መንግሥታችው እንደደረሰው ተናግረዋል። ኃላፊው በኢትዮጵያ መንግሥት የተሾመለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የትግራይ ባለሥልጣናት ሰዎችን በግዳጅ ለውትድርና እንደሚመለምሉና ፈቃደኛ ያልሆኑ ወላጆችን እንደሚያስሩ የተረጋገጠ ማስረጃ እንዳለው ለሮይተርስ በሰጠው ምላሽ ገልጿ።

ሁለት የተማረኩ የትግራይ ተዋጊዎች በአጎራባች አፋር ክልል በሚገኝ ሆስፒታል ሆነው በየካቲት ወር እንደተናገሩት ደግሞ የግዳጅ ምልመላው የጀመረዉ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ ነው። የግዳጅ ምልመላው በጥር ወር ላይ እየጨመረ መምጣቱን ስድስት የትግራይ ነዋሪዎች ለሮይተርስ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም ጓደኛ፥ ወይም የቤተሰብ አባሎቻችው በአስገድዶ ምልምላ ወቅት እንደታሰሩባችው ጠቅስዋል።

የ18 ዓመቱ አልዩ አንድ ስሙን የማያውቀው የአካባቢው ባለሥልጣን እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ኅዳር 10 ቀን እንዳባጉና በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ እንዴት እንደመጡ አስርድቷል። ሮይተርስ የአልዩን የአባት ስም ለእርሱና ለቤተሰቡ ደህንነት ሲል መደበቁን አመልክቷል።

“እናቴ እንደምትታሰርና ቤተሰቤ ከ 10,000 እስከ 20,000 የኢትዮጵያ ብር እንደሚቀጣ ነገረኝ። ጦሩን እንድቀላቀልም አስገደደኝ” ብሏል አልዩ።

አፋር ውስጥ ጭፍራ ከምትባል ከተማ አቅራቢያ እግሩን ከተመታ ወዲህ አልዩ ዱብቲ ሆስፒታል ይገኛል። አልዩም ሆነ ሌላኛው ምርኮኛ በአንድ ክፍል ውስጥ የተያዙ ሲሆን ቃለመጠይቁም በአፋር ክልል ባለስልጣናት የተፈቀደ ነበር። ሁለቱም እስርኞች ቃለ መጠይቁን በፈቃደኝነት ያደረጉ ሲሆን ጠባቂዎች ወይም ባለሥልጣናት በቃለ ምልልሱ ወቅት አልተገኙም ብሏል ሪፖርቱ።

“እናቴ እንድትታሰር አልፈለኩም”

ሌላኛው ምርኮኛና የመቀሌ ነዋሪ የነበረው የ18 ዓመቱ ፊሊሞን ባልሥልጣናት በኅዳር ወር በመንደራቸው በጠሩት ስብሰባ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ሰው እንዲያዋጣ ካለዛ ግን የገንዘብ ቅጣት ወይም እስር እንደሚጠብቃቸው ነግረውናል ብሏል። ፊሊሞን የትኞቹ ባለስልጣናት ስብሰባውን እንደጠሩ ግን አልጠቀሰም።

“ጦሩን ተቀላቀልኩ። እናቴ ዘብጥያ እንድትወርድ አልፈለኩም” ሲል በአንድ የደፈጣ ውጊያ ወቅት የግራ እግሩን ያጣው ፊሊሞን ለሮይተርስ ተናግሯል።

እግሩን ከተመታ በኋላ ለዘጠኝ ቀናት በብስኩትና በወንዝ ውሃ ቆይቶ በኋላም አንድ ገበሬ ለኢትዮጵያ ሰራዊት አሳልፎ ሰጥቶታል። ሰራዊቱም በጊዜያዊ ሆስፒታሉ ሲያክመው ከቆየ በኋላ እግሩ ጋንግሪን ስለያዘው ሊቆረጥ በቅቷል።

“ጦርነት አስክፊ ነው። የገዛ ጓደኞችህን አስከሬን ጆፌ አሞራ ሲበላው ታያለህ” ሲልም በለሆሳስ ድምጽ አክሏል።

የሁለቱ ምርኮኞች ምስክርነት በሌሎች ስድስት የትግራይ ነዋሪዎች ተደግሟል። ሁሉም በቀል እንዳይደርስባቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል። እያዳንዳቸውም የራሳችው የቤተሰብ አባል ወይም ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላቸው የታሰሩባችው ሰዎች እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ እንዳለው በጥር ወር ላይ በተደረገ የአካባቢው ስብሰባ ላይ በራሪ ወረቀቶች እንደተበተኑና ወረቀቶቹም ነዋሪዎች እንዳይደበቁ ጥሪ ያደርጋል። “አሁኑኑ ውደ ማሰልጠኛ በመሄድ ለእናት ሀገራቸሁ አስተዋጽዎ አድርጉ” ይላል ሮይተርስ የተመለከተው ሰነድ።

ሰነዱም በጥር 9 ቀን የተጻፈ ሲሆን የትግራይ ክልል መንግሥትና የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ማኅተም አርፎበታል። እውነታኛነቱን ግን ሮይተርስ ማርጋገጥ አልቻለም።

ስሙን መግለፅ ያልፈለገው ሌላው ነዋሪ እና አዲስ ትዳር መስራች ደግሞ እርሱ ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት ነፍሰጡር ሚስቱን በሚያዚያ ወር ከተደረገ አንድ አስገዳጅ ስብሰባ በኋላ እንዳሰሯት ተናግሯል። በስብሰባው ላይ በፖሊስ ጣቢያ የነበሩ ሰዎችም እርሱ ሰራዊቱን ካልተቀላቀለ ሚስቱ እንደማትለቀቅ ነግረዋታል ብሏል።

ሌሎች እስርኞች ነፍሰጡር ሴትን ማሰር አሳፋሪ ምሆኑን ለጠባቂዎቹ ከተናገሩ በኋላ ለቀዋታል ሲል አከሏል።

የመዋጋት ፍላጎት መቀነስ

በመጋቢት ወር ላይ የ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግሥት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ብዙም አለመረጋጋት የታየበት ሁኔታ እና አልፎ አልፎም የጦርነት ዘገባዎች ተስትውለዋል። አዲስ አበባን ለመያዝ የቆረጡት የትግራይ ትዋጊዎችም ወደ ክልላቸው ተመልሰዋል። የግዳጅ ምልመላው ግን ህወሃት ወደ ውጊያ ለመመልስ እየተዘጋጀ መሆኑን ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ እየቀነሰ የመጣውን የመዋጋት ፍላጎት ያመለክታል።

ፕ/ር ክንደያ ግን ይህን ያስተባብላሉ ፤ “ጦራችንን የሚቀላቀሉ ሰዎች እጥረት ኖሮብን አያውቅም። አንዳንድ ፈቃደኞቻችንም ውጊያን በማይመለከቱ ጉዳዮች እንዲያግዙ ወደመጡበት መልሰናል።” ብለዋል።

አያይዘውም “ሁሌም ለሰላም ዕድል መስጠት እንመርጣለን። ነገር ግን ይህ የማይቻል ከሆነና ጦርነቱ እላያችን ላይ ከተጫነብን እራሳችንን ለመከላከል መዘጋጀት እንዳለብን ግልጽ ነው። ማንኛውም የምናደርገው እንቅስቃሴና ዝግጅትም በዛ መልኩ መታየት አለበት።” ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ከኅዳር 2020 እስከ ሰኔ 2021 ዓ.ም የመንግሥት ኃይሎች ትግራይን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት የጅምላ ግድያና የቡድን አስገድዶ መድፈር እንደፈጸሙ በደርዘን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተናግረው ነበር። መንግሥት በበኩሉ ጥቂት ወታደሮችን መያዙን እና ነገር ግን ሪፖርቶቹ የተጋነኑ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

የመብት ጥሰቶቹም ከትላልቅ ከተሞች እስከ ጥቃቅን መንደሮች የተፈጸሙ ሲሆን፥ ሰዎች በፈቃደኝነት የትግራይን ጦር እንዲቀላቀሉና የመንግሥት ኃይሎችን እና ተባባሪዎቻቸውን በ2021 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከትግራይ ለማሰወጣት እንዲችሉ ኃይል ሰጥቷችዋል።

ሌላ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነዋሪ ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ወደ አጎራባች አማራ ክልል ከገቡና ከዛም በደም አፋሳሽ ጦርነት ለቀው እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ የመዋጋት ፍላጎት መቀነሱን ተናግሯል።

“ከዚህ በፊት በርካታ ወጣቶች ቤታችን የምንቆይ ከሆነ በመንግሥት ወይም በአማራ ጦር እንገደላለን በሚል ወይም የደረሰውን የመብቶች ጥሰቶች ለመበቀል የትግራይን ጦር ተቀላቅለው ነበር። አሁን ግን ያንን ለማድረግ ጥቂት ፈቃደኞች ናችው ያሉት።”

የትግራይ መንግሥት እጅግ አስፈላጊ የሆነው የምግብ ዕርዳታ እንዲገባ ቢጠብቅም እሰካሁን የደረሰው ግን እጅግ ጥቂት መሆኑን ይገልጻል።

“ማዕከላዊ መንግሥት ዕርዳታ እንዳይገባ ማገዱን ቀጥሎበታል። ለወረራም እየተዘጋጅ ነው” ይላሉ የህውሃቱ መሪ ዶ/ር ደብረፂዎን ገብረሚካኤል። የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ግን ዕርዳታ መታገዱን ያስተባብላሉ።

ሴትና ወንድ ህጻናት ኢላማ ሆነዋል

በመቀሌ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ የ70 አመቷ አዛውንት ጎረቤቱ ሴት ልጇ ጦሩን እንድትቀላቀል ለማስገድድ በሚያዚያ 16 ቀን አስረዋታል ብሏል። ግለሰቡ የአጎት ልጁንም ወንድ ልጁን እንዲመዘገብ ለማስገደድ ሲሉ አስረውታል ሲል አክሏል።

በሮይተርስ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ነዋሪዎች በመቀሌ ሽሬ ውቅሮ አዲግራት እና አድዋ እስራት እንደነበር ተናግርዋል። በርካታ ምንጮች በመቀሌና ሽሬ እስሩን ያረጋገጡ ሲሆን በሌሎቹ ሦስት ከተሞች ያሉ ሰዎችን ግን ማነጋገር አልተቻለም ብሏል ሪፖርቱ።

ታሳሪዎቹ በአብዛኛው በፖሊስ ጣቢያ እንደሚያዙ ታሳሪዎቹን የጎበኙ ሁለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።ሪፖርቱ በመቀጠልም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አስተያየት ለመስጠት በቂ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። በህወሃት ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችም ለጋዜጠኞች እና ተመራማሪዎች ክፍት አይደሉም ብሏል።

ሌላ በቀልን በመፍራት ስሙን የደበቀ የመቀሌ ነዋሪም የ17 ዓመት ሴት የቤተሰብ አባል “የአካባቢው ባለሥልጣናት በሌሊት ቤቷ ከመጡ በኋላ ጦሩን ለመቀላቀል ተገዳለች” ሲል ተናግሯል።

“ሁሉም ኢላማ ነው። ሴትና ወንድ ልጆችም።” ካለ በኋላ “ይህ አዲሱ ግን የተለመደው ተግባር ነው።”

XS
SM
MD
LG