በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በካኩማ እና ዳዳብ የሚገኙ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮዎች ዝግ መሆናቸዉን ስደተኞች ይናገራሉ


ሰሜን ምስራቅ ኬንያ ያለው ካኩማ የስደተኞች መጠለያ /ፋይል ፎቶ/
ሰሜን ምስራቅ ኬንያ ያለው ካኩማ የስደተኞች መጠለያ /ፋይል ፎቶ/

የኬንያ መንግስት በዳዳብና ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኘውን መስሪያ ቤት መዝጋቱን በጣቢያው የሚኖሩ ስደተኞች ተናገሩ። ስደተኞቹ እንደሚሉት የጣቢያው አስተዳደር የሆነዉ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ቅርንጫፍ ከባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁሟል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ የኬንያ መንግስት ዉሳኔዉን እንዲያጤን ጠይቋል። የኬንያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠው መግለጫ የለም።

ከባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ አንስቶ በካኩማ እና ዳዳብ የሚገኙ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮዎች ዝግ መሆናቸዉን በሁለቱ ጣቢያዎች የሚኖሩ ስደተኞች ለአሜርካ ድምጽ ተናገረዋል። እንደ ስደተኞቹ የጣቢያውአስተዳደር፣ የስደተኞችን የምዝገባና የሰፈራ መረሃ ግብር የሚያስፈጽመዉን ቢሮ በመዘጋቱ፤ በተለይ አዲስ ተመዝጋቢ ስደተኞች በመቸገር ላይ መሆናቸዉን ይናገራሉ።

በቱርካና ግዛት በሚገኘዉ የካኩማ የስደተኞች ሰፈር የኬንያ ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ቅርንጫፍ የኦሮሚኛ ቋንቋ አስተርጉሚ የሆነዉ ሁሴን እንደሚለዉ፣ በባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ናይሮቢ ከሚገኘዉ ዋና መሥርያ ቤት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዉ ሥራ እንዲናቆም ትዕዛዝ በመተላለፉ ቅርንጫፍ ቢሮዉ ዝግ መሆኑን ይናገራል።

"የኬንያ ስደተኞች ቢሮ ሥራ በማቆሙ ዛሬ ስራ የለም፣ ወደ ሥራ የምንመለስ ከሆንን እንነግራቹኃለን ስለዚህ ወደ ቢሮ እንዳትመጡ የሚል ነገር ነዉ የነገሩን እና አሁን እነሱ የሚሉንን ነገር ነዉ እየጠበቅን ያለነዉ። ነገር ግን ስደተኞች አሁንም በመምጣት ላይ ናቸዉ በተለይ ከሱዳን፣ እንደዉም አሁን በስደተኞች የቅበላ ማዕከል ዉስጥ በጣም ብዙ ስደተኛ ነዉ ያለዉ፣ ሌላ ደግሞ ከድምበር የሚመጡ ስደተኞችም አሉ ለእነኚህ ሁሉ የቢሮዉ ሥራ በመቆሙ ጉዳያቸዉ መፈጸም አልተቻለም።" ብለዋል።

የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ በዚህ በ2016 መጀመርያ አዲስ ተመዝጋቢ ስደተኞችን መዝግቦ የተገን ጠያቂነት መብት ዉሳኔ ለስደተኞች የመስጠትሥራን ከ(UNHCR) የተረከበ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ፣ የጣቢያ አስተዳደር ሥራ፣ የሰላምና መረጋጋት ሥራንም በስደተኞች ሰፈር ዉስጥ የማስፈጸም ኃላፍነት ያለዉ የመንግስት አካል ነዉ።

በሁለቱ ትላልቅ ጣቢያዎች ዉስጥ የሚኖሩት ስደተኞች ወደ ተለያዩት የኬንያ ግዛቶች ለመንቀሳቀስ ፍቃድ የሚሰጣቸዉም ይህ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ሲሆን፣ በተለይ ለትምህርትና ለህክምና ወደ ናይሮቢ እንዲሁም ወደ ሌሎች የኬንያ ከተሞች የሚጓዙ ሰዎች በዚህ የተነሳ እየተቸገሩ እንዳሉ ይናገራሉ።

መንግስቱ ጭምዴሳ በዳዳብ የስደተኞች ሰፈር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ነዉ፣ መንግስቱ በናይሮቢ የኬንያታ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክ ተማሪ ሲሆን፣ወደ ናይሮቢ ሄዶ ትምርቱን ለመቀጠል ሲል የጉዞ ፍቃድ ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዉ ቢመላለስም ጉዳዬን የሚፈጽምልኝ ሰዉ ማግኘት አልቻልኩም ሲል ይናገራል።

"እኔ እራሴ አሁን ተማሪ ነኝ ወደ ናይሮቢ ሄጄ መማር ነዉ የምፈልገዉ፣ ኬንያታ ዩኒቨርስቲ ነዉ የምማረዉ፣ ያዉ ሙቭመንት ፓሥ (የጉዞ ፍቃድ ወረቀት) ከ DRA (የኬንያ ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ) ስለማገኝ፣ ባለፈዉ ዓርብ እኔ እራሴ ሄጄ ነበር እዛ፣ ብዙ ጊዜ ቆየን መጨርሻ ላይ ስንጠይቃቸዉ (DRA Officially) መንግስት ኦፊሳቸዉን ዘግተዋል ከናይሮቢ ጀምሮ እስከዚህ፣ ስለዚህ እኛ ለእናንተ ወረቀት መስጠት አንችልም አሉን ተመለስን፣ ማለት እንግዲህ እኔ አሁን አጓጉል ላይ ነኝ ማለት ነዉ ትምህርቴን መከታተል አልቸልኩም ትምህርት ተከፍቷል። ስለዚህ ያለ ወረቀቱ ከዚህ ወደ ናይሮቢ ይቅርና ከዳዳብ ራሱ ወጣ ብለህ መንቀሳቀስ አትችልም ማለት ነዉ።" ብሏል።

ኬንያ ለሩብ መቶ ዓመት ለብዙ ተገን ፈላጊዎች ከለላ በመሆን በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጉልህ ሚና ትጫዉታለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ቃል አቀባይ ኤድሪያን ኤድዋርድስ

የኬንያ መንግስት ዉሳኔን በማስመልከት ዋና መቀመጫዉን በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ያረገዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ (UNHCR) ትላንት መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫዉም የኬንያ መንግስት ዉሳኔዉን እንደገና እንዲያጤነው ተማጽነዋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ኤድሪያን ኤድዋርድስ “ኬንያ ለሩብ መቶ ዓመት ለብዙ ተገን ፈላጊዎች ከለላ በመሆን በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጉልህ ሚና ትጫዉታለች" በማለት ተናግረዋል። አቶ ኤድዋርድስ አክለዉም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠትም ድርጅታቸዉ ከኬንያ መንግስት ጋር እንደሚሰራም አሳዉቀዋል። በሁለቱ ጣቢያዎች የሚኖሩ ስደተኞች ዉሳኔዉን በማስመልከት ህይወታቸዉ ስጋት ላይ መሆኑን ሲናገሩ በተለይ ከትዉልድ ሃገራቸዉ እስራትንና ጦርነትን በመሸሽ በስደተኞች ጣቢያው ተጠልለዉ ላሉት ይህ አስደንጋጭ ዉሳኔ ነዉ ይላሉ።

የኬንያ መንግስት በበኩሉ በሃገሪቱ ላይ የተፈጸሙት የሽብር ተግባራት የተጠነሰሱት በስደተኞች ሰፈር ነዉ በማለት የብሄራዊ ደህንነት ፈተና እንዳለበት ያስረዳል። የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ካራንጃ ኪቢቾ ከሶስት ዓመታት በፊት በዌስት ጌት የገበያ ማእከል የደረሰዉ የሽብር ጥቃት በዳዳብ የስደተኞች ሰፈር የተወጠነ መሆኑ የመረጃና የደህንነት ቢሮዋችን በቂመረጃ አለዉ፣ ስለዚህ ምንም እንኳን ጣቢያውን መዝጋት የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቢቆም፤ በቅድምያ ለሃገራችን ዜጎች ተጠያቂነት ስላለብን ከዚህ ዉሳኔ ደርሰናል በማለት ‘The Independent’ ለተባለ ጋዜጣ ተናግረዋል። ኬንያ ከ600 ሺህ በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ በአፍሪካ ሁለተኛ ሃገር ናት።

“ስድተኞችን ያለፈቃዳቸው መመለስ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ይጻረራል” የቀድሞ ሶማሊያዊ ዲፕሎማት

ሶማሊያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጦርነት ስትታመስና ዜጎቿ ሲሰደዱ ቆይታለች። በእርስ በርስ ጦርነቱ ሳቢያ ለነፍሳቸው በመስጋት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ጎረቤት ኬንያና ኢትዮጵያ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሀገሮች ከተሰደዱት በተጨማሪም፤ ከአምስት አመታት በፊት የተከሰተውን ድርቅና ረሃብ ሽሽት ወደ ኬንያ የገቡት ሶማሊያዊያን እጅግ ብዙ ናቸው።

በወቅቱ ኬንያ ከ600ሽህ በላይ ሶማሊያዊያን ስድተኞችን አስጠልላ ነበር። የኬንያ መንግስት በወቅቱ ለሶማሊያዊያን የሰጠውን ጥገኝነትና ዋስትና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት UNHCRን ጨምሮ ሌሎችም ያወደሱትና አብረው የሰሩበት ጉዳይ ነበር።

የኬንያ መንግስት በተደጋጋሚ በመላ ሃገሪቱ እየደረሱ ያሉ የሽብር ጥቃቶች፤ የስደተኞች ጣቢያዎችን አማክለው፤ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፉ ያሉ ሴራዎች እንደሆነ በመጥቀስ፤ የስደተኞች ጣቢያዎቹ የሽብርተኞች መናኸሪያ ሆኑብን በማለት፤ ስደተኞች በፈቃድ እንዲመለሱ ሲያሳስብ ቆይቷል።

በኬንያ የቀድሞ የሶማሊያ አምባሳደር ሞሀመድ አሊ ኑር ስደተኞችን በፈቃዳቸው ካልሆነ በስተቀስ ሸሽተው ወደመጡባቸው አካባቢዎች መመለስ፤ የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ይጻረራል። “በኛ በሶማልያውያንና በኬንያ መንግስት መካከል የUN በስደተኞች ላይ የተቀመጠውን ስምምነት እንጋራለን። ስምምነቱም ስደተኛን ወደ መጣበት ያለፍላጎቱ ላለመመለስ ነው። እንደማምነው ኬንያም የገባችውን ቃል ትጠብቃለች የሚል እምነት አለኝ።” ብለዋል።

“በኬንያ የሱማሌ አምባሳደር ሆኜ ባገለገልኩበት ወቅት የስደተኞች መጠለያ ቦታዎችን በተደጋጋሚ ጎብኝቻለሁ። በመጠለያ የሚገኙትን ሱማልያውያን ስደተኞች ለጊዜው እንጂ ነዋሪነታቸው እስከመጨረሻው በመጠለያ ለመኖር አይፈልጉም። ብዙዎቹ ወደትውልድ ሃገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ ለዚህም ወደ 10,000 የሚጠጉ ሱማልያውያን ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ሃገርን የሚጠላ ማንም የለም፤ የተሻለውም በሃገር መኖር ነው።

በሰው ሃገር መኖር ምቾትን አይሰጥም። በኬንያ ቦታ ሆኜ ራሴን ሳየው ለብዙ ስደተኞች ጊዜያዊ መኖሪያ በመሆን ትልቅ ሸክምን ለአመታት ስታስተናግድ ቆይታለች። አሁን ከግማሽ ሚልየን በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በኬንያ የስደተኞች ካምፕ ከሃያ አመታት በላይ በመኖር ላይ ይገኛሉ።” አምባሳደር ሞሀመድ አሊ ኑር በቀጣይነት ያነሳሁት ጥያቄ የኬንያ መንግስት በተደጋጋሚ የሚደርሱባቸው የሽብር ጥቃቶች በስደተኞች ሰፈሮች በኩል የተሻገሩ ናቸው በሚሉ ስጋቶች ናቸው “ሃገሪቱን በሽብር ከሚያናውጡት አሸባሪዎች ጋር በመጠለያ የሚኖሩት ስደተኞች በፍፁም መተባበር የላቸውም።

በመጠለያ የሚገኙትን ስደተኞች ከነዚህ ሽብርተኞች ጋር አብሮ መፈረጅም ትክክል አይመስለኝም። እነዚህ አሽባሪዎች የሁላችንም ጠላቶች ናቸው፤ እንሱንም ለመፋለም በጋራ እንሰራለን።” በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች መካከል፤ መሬታቸውና ቤታቸውን ጥለው ከወጡ በለተይ ከአስር እስከ ሃያ ዓመታት የሆኗቸው፤ ንብረት አልባ መሆናቸው ነው።

አምባሳደሩ የሶማሊያ መንግስት የያዘውን ጥረት ሲያስረዱ “ ከሃያ አመት በፊት ወደሌላ ሃገር የተሰደዱት ሱማሊያውያን በሱማሌ የነበራቸው መሬትና መኖሪያ ቤታቸው ተወስዶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የሱማሌ መንግስት ንብረታቸውን በተተኪ መልሶ ለመስጠት ዝግጁ ነው።” ብለዋል።

የጸጥታና ደህንነት ጥናት ባለሙያዎች ለረጂም ጊዜ ከሶማሊያ ወጥትተው የቆዩ ስደተኞች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ፤ የመሬት፣ ውሃና ግጦሽ አጠቃቀምና ይዞታ ግጭቶችን ሊያጭሩና፤ የሀገሪቱን ጸጥታ ሊያደፈርሱ ይችላሉ በሚል ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

የስደተኞች ጉዳይ ቢሮዎች ዝግ መሆናቸዉን የያዘ ሙሉ ዘገባዉን ገልሞ ዳዊት ከናይሮቢ አድርሶናል። በተጨማሪም ሔኖች ሰማእግዜር ከየቀድሞው የሶማልያ አምባሳደር ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ የያዘውን ዝርዝር ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።

በካኩማ እና ዳዳብ የሚገኙ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮዎች ዝግ መሆናቸዉን ስደተኞች ይናገራሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:41 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG