በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬንያ ስደተኛ መቀበል ልታቆም ነው


የኬንያው ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ መንደር በከፊል
የኬንያው ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ መንደር በከፊል

የኬንያ መንግሥት በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ሠፈሮችን ለመዝጋት መወሰኑን አስታወቀ።

የኬንያ መንግሥት በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ሠፈሮችን ለመዝጋት መወሰኑን አስታወቀ።

ከሃገሪቱ የሃገር ግዛት ሚኒስቴር ከትናንት በስተያ፤ ዓርብ የወጣ መግለጫ እንዳመለክተው የኬንያ መንግሥት ለሃገሪቱ ፀጥታና መረጋጋት ሲል ይህንን እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን አስታውቋዋል።

መግለጫው የኬንያ የስደተኞች ቢሮ መዘጋቱን ያስታወቀ ሲሆን አንድ የቢሮው ባልደረባ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል ግን ጉዳዩ ሰፊ ማብራሪያ ስላልተሰጠበት በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ስደተኞች የእርምጃው ሁኔታ በግልፅ እስኪታወቅ በርጋታ እንዲቀመጡ ማሳሰባቸውን ናይሮቢ የሚገኘው ሪፖርተራችን ገልሞ ዳዊት ዘግቧል፡፡

የኬንያ የሃገር ግዛት ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫው በተለይ የአልሻባብንና የሌሎች የሽብር ቡድኖችን ጥቃት ለመከላከል ሲል ሃገሪቱ ስደተኞችን ማስተናገድ ለማቆምና መንግሥቷም እዚያ ያሉ ስደተኞችን ለመመለስ መወሰኑን አስታውቋል።

መግለጫው አክሎም ዳዳብ ና ካኩማ የሚባሉት ሁለቱ ግዙፍ የስደተኞች መጠለያ ሠፈሮች ከ30 ዓመታት በላይ ያሉ በመሆናቸው የሚኖሩባቸው ስደተኞች ለሃገሪቱ ሸክም ሆነዋል ብሏል።

“ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ለስደተኞቹ ቋሚ መፍትሄ አልሰጠም” ሲልም መሥርያ ቤቱ ቅሬታውን ገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር - ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. የኬንያ ቅርንጫፍ በበኩሉ መግለጫው ለድርጅቱም አዲስ በመሆኑ ስለሁኔታው በመጭው ሣምንት ውስጥ ከኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያይ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጿል።

ኬንያ ከሚገኙት ስደተኞች የሚበዙት ሶማሊያዊያን ሲሆኑ ኬንያ መንግሥት ከሶማሊያ መንግሥትና ከዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. የኬንያ ቅርንጫፍ ጋር በመሆን ፈቃደኛ የሆኑ የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የመመለስ ፕሮግራም መጀመሩ ታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ባለፈው ሚያዝያ ብቻ ከካኩማ የስደተኞች ሠፈር ወደ ሰላሣ የሚጠጉ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ሶማሊያ እንዲመለሱ ማድረጉ ተገልጿል።

የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የመመለስ መርሃግብር በታኅሣስ 2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁንም ከ13 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች ሰላማዊ ወደ ሆኑ የሶማሊያ አካባቢዎች እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል።

ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው የመመለሱ ሥራ መጓተቱን በትናንት መግለጫው ያሳወቀው የኬንያ የሃገር ግዛት ሚኒስቴር የሃገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ላይ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረኮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየቱን ጠቁሟል።

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ባስቸኳይ ጣልቃ ካልገባ የኬንያ መንግሥት ሁለቱንም የስደተኞች መጠለያ ካምፖችን በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል ሲል የኬንያ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መርኃግብር ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. የኬንያ ቅርንጫፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኬንያ ውስጥ ከ600 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን ሰላሣ ሺህ የሚሆኑት የኢትዮጵያዊያን ናቸው።

XS
SM
MD
LG