ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወረራ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በዋና ከተማዋ ኪየቭ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል። ኒው ወርክ ታይምስ “የእሳት ፍንጥርጣሪ” በኪየቭ ሰማይ ላይ ሲወርድ የሚሳይ የተረጋገጠ ቪዲዮ እንዳለው ዘግቧል። ቪዲዮው ከፍንዳታው በፊት ከምድር ወደ ሰማይ ተወንጫፊ ሁለት ሚሳኤሎች ሲተኮሱ እንደሚያሳይም አክሏል።
ከፖላንድ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው፣ በርካታ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች በጊዜያዊነት በሚገኙበት ምዕራብ ዩክሬን በምትዋሰነው ሊቪቭ ከተማ የአደጋ ጊዜ ማንቂያዎች እንደተሰሙ ታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሎይድ አውስቲን ትናንት ምሽት፣ ከቤላሩስ የተነሱ የሩሲያ ወታደሮች ከኪየቭ 32 ኪሎሜትር ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። በሰሜን ዩክሬን የሩሲያ ወታደሮች የቼርኖቤል ኑዩክሌር የኃይል ጣቢያን በተመሳሳይ ተቆጣጥረዋል።
“ይህ በመላ አውሮፓ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው!’’ ብለዋል የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሜር ዘለንስኪ ።
ቼርኖቤል በዓለም እጅግ አሰቃቂ የሚባለውን የኒዩክሌር ፍንዳታ የተከሰተበት ሥፍራ ነው። በአውሮፓዊያኑ 1986 ከተከሰተው አደጋ ወዲህ የጣቢያ ዙሪያ የሰው ልጆች መኖሪያ መሆኑ ቀርቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፀረ -ጦርነት ተቃዋሚዎች ሞስኮ እና ሴንት ፒትርስበርግን ጨምሮ ሩሲያ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ሰልፍ ወጥተዋል። ይሄን ተከትሎ ቢያንስ 1700 ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትናንትናው ዕለት በሩሺያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥለዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን “ወራሪ” ብለው የጠሩት ፕሬዚዳንቱ ከቡድን ሰባት ሀገራት እና ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር) ሀገራት ተወካዮች ጋር የርቀት ስብሰባ ካደረጉ በኃላ ባሰሙት ንግግር የማዕቀቡን ይዘት አብራርተዋል።
አዲሱ ማዕቀብ የሩሲያ ባንኮችን፣ ጫና ፈጣሪ ባለጸጋዎችን፣ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ዘርፎችን እና የውጭ ንግድ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ባይደን ጠቁመዋል።
አዳዲሶቹ እርምጃዎች የሩሲያን ወደ ፋይናንስ እና ለኢኮኖሚያዋ ቄልፍ የሆኑ ቴክኖሎጂ መደራሻዎች ላይ ጫና በማሳደር፣ በሚመጡት ዓመታት ኢንደስትሪያው አቅሟን እንደሚያዳክሙ ባይደን ተናግረዋል።
እንግሊዝ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የኔቶ አጋሮች፣ ተጨማሪ ማዕቀቦችን በትናንትናው ዕለት ጥለዋል። የማዕቀቡ ውጤት ከመቅጽበት በዓለም ገበያ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የአክሲዮን ገበያዎች ሲነክቱ፣ የሸቀጦች ዋጋ ደግሞ አሻቅቧል። ባይደን አሜሪካዊያን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደሚገጥማቸው በጠቀሙበት ንግግራቸው “ለዚህ ወረራ ምላሽ ሳንሰጥ አንቀርም። አሜሪካ ለነጻነት ትቆማለች። የእኛ ማንነት ይሄው ነው!” ብለዋል።