በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጥቃት 40 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ


ነዋሪዎች ዩክሬን ዋና ከተማን ኪየቭን ለቀው ሲወጡ፣ የትራፊክ መጨናነቅ እእአ ፌብሩዋሪ 24/2022
ነዋሪዎች ዩክሬን ዋና ከተማን ኪየቭን ለቀው ሲወጡ፣ የትራፊክ መጨናነቅ እእአ ፌብሩዋሪ 24/2022

ሩሲያ ዛሬ ማለዳ ጀምሮ በዩክሬን ላይ ጥቃት እንደከፈተች ታውቋል። ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሌሎች ሀገራት ጣልቃ እንዳይገቡ እያስጠነቀቁ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ ምዕራባዊያኑ የዩክሬን አጋሮች ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ፣ አዲስ ዙር ጠንካራ መዓቀብ እንደሚያከታትሉ አስታውቀዋል። የአሁኑን የሩሲያን ጥቃትም አውግዘዋል።

ፑቲን ጦራቸው ጥቃት መጀመሩን ይፋ በዳረጉበት በቴሌቭዥን የተላለፈ ንግግራቸው፣ በምስራቅ ዩክሬን የተጀመረው ዘመቻ ከዩክሬን በኩል ለተደቀኑ አደጋዎች አጸፋ እንደሆነ ተናግረዋል። ጦራቸው በዶንባስ ግዛት የሚወስደውን እርምጃ የሚቃወሙ “አይተውት የማያውቁት ውጤት” እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቀዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሜር ዘለንስኪ የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬንን የጦር ግንባታዎች እና የድንበር ዘቦችን ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል። ህዝባቸው ተረጋግቶ በቤቱ እንዲቆይ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ ፣ መንግሥታቸው “የማርሻል ህግ” ተብሎ የሚጠራውን የጦር ሰራዊቱ የሲቪል መስሪያቤቶችን ተክቶ የሚሰራበትን ህግ እንደተገበረም አስታውቀዋል።

“አትደናገጡ፣ ጠንካሮች ነን፣ ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነን። ዩክሬናዊያን ስለሆን ሁሉም ነገር እናሸንፋለን!’’ ብለዋል ዘለንስኪ ።ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የነበራትን ግንኘት እንዳቋረጠች እና መንግስታቸው “ሀገሩን ለመከላከል የሚሻ ማንኛውንም ሰው” እንደሚያስታጥቅ አስታውቀዋል።

የዩክሬን ጦር ከዛሬ ሀሙስ ጠዋት ጀምሮ የሩሲያ ጦር በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በሮኬት እንደደበደበ አስታውቋል። የፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ረዳት በጥቃቱ 40 ሰዎች እንደተገደሉ ለዘጋቢዎች ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የአሁኑ ጥቃት ለሚያስከትለው ሞት እና ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂ እንደምትሆን ተናግረዋል። ሀገራቸው እና አጋሮች በህብረት እና በጠነከረ መልኩ ለጥቃቱ ምላሽ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

ዛሬ ማለዳ ከቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች ጋር በስልክ የተነጋገሩት ባይደን፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ከረር ያለ መዓቀብ በሩሲያ ላይ እንደሚጥሉም አክለዋል።

XS
SM
MD
LG