በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት አደረሰች - ባይደን ፑቲንን 'ቀድመው የተዘጋጁበት' ባሉት ጦርነት ከሰዋቸዋል


የወደመ ራዳርና ሌሎች መሳሪያዎች በዩክሬን ወታደራዊ ተቋም በማሪዩፖል፣ ዩክሬን/ሐሙስ የካቲት 17/2014 ዓ.ም
የወደመ ራዳርና ሌሎች መሳሪያዎች በዩክሬን ወታደራዊ ተቋም በማሪዩፖል፣ ዩክሬን/ሐሙስ የካቲት 17/2014 ዓ.ም

ሩሲያ በዛሬው ዕለት በዩክሬን ላይ ጥቃት ያደረሰች ሲሆን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሌሎች ሀገራት ጣልቃ እንዳይገቡ አስጠንቅቀዋል። የዩክሬን አጋር የሆኑት የምዕራብ ሀገራት ሩሲያ ያደርሰችውን ጥቃት አውግዘው ለዩክሬን ድጋፋቸውን እንደሚሰጡና አዲስ ዙር ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ገልፀዋል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቭዥን ባስተላለፉት መልዕክት ከዩክሬን ለተደቀነባቸው ሥጋት ምላሽ ወታደራቸውን ወደ ምስራቅ ዩክሬን ለማሰማራት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

ፑቲን ውሳኔያቸው የተላለፈው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦርነት እንዳይነሳ ለማስጣል አስቸኳይ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት ሲሆን በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ሩስያ በዶንባስ ቀጠና የምትወስደውን እርምጃ የሚቃወም እስከዛሬ አይተውት የማያውቁት ምላሽ ይደርስባቸዋል በማለት አስጠንቅቀዋል።

በተመሳሳይ ሰዓት በርካታ ፍንዳታዎች ከዩክሬን ዋና መዲና ኪየቭ የተሰማ ሲሆን የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቩለድሚር ዚለንስኪ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ወታደራዊ ተቋማት እና በድምበር የሚገኙ ጠባቂዎች ላይ ጥቃት ማድርሷን አስታውቀዋል።

ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት በኪየቭ የሚገኙ ሁለት የአውሮፕላን ማረፊያዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጥቃት ኢላማ ተደርገዋል። የተወሰኑት ሮኬቶች ደግሞ በዩክሬን ኃይሎች ወደ ድሮኖቹ የተተኮሱ መሆናቸውም ተገልጿል። ሩሲያ ምናልባት የአየር መቃወሚያዎችን ኢላማ በማድረግ ወደፊት ለምታደርሰው የአየር ጥቃት ሁኔታዎች እያመቻቸች ሊሆን ይችላል ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ጥቃቱን አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት ምላሽ የዩክሬን ሕዝቦች 'ባላነሳሱት እና ትርጉም በሌለው የሩሲያ ወታደሮች ጥቃት' ስቃይ እየደረሰባቸው ነው ብለዋል።

አክለውም ከሌሎች የቡድን ሰባት ሀገራት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ፣ ሩሲያ በዩክሬን እና በዓለም ሰላምና ፀጥታ ላይ ላሳየችው አላስፈላጊ ጠብ ጫሪነት በቀጣይ የሚሰጧቸውን ምላሾች እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG