በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፍሪካ በዩክሬን ወረራ ጉዳይ ዝምታን መርጣለች


ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የአፍሪካ መሪዎችና ባለሥልጣኖች ጋር የሩሲያ - አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ በሶቺ በ2019 በተካሄደ ወቅት።
ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የአፍሪካ መሪዎችና ባለሥልጣኖች ጋር የሩሲያ - አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ በሶቺ በ2019 በተካሄደ ወቅት።

ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ጉዳይ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኬንያ አምባሳደር ባለፈው ሰኞ ከተናገሩት በስተቀር አፍሪካ እስካሁን ዝምታ ላይ ነች።

ብዙ አፍሪካዊያን ከሩሲያ የኃይል እርምጃ ጋር ባይስማሙም የአህጉሪቱ መንግሥታት ግን በዓለምአቀፍ ደረጃ ያላትን አቅም እንደሚገነዘቡ ተንታኞችን የጠቀሰ የቪኦኤ የናይሮቢ ሪፖርተር ሞሃመድ ዩሱፍ ዘገባ ይናገራል።

ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ሩሲያ በሃገራቸው ላይ ያካሄደችውን ወረራ ተቃውሞ እንዲያግዛቸው በኬንያ የዩክሬን አምባሳደር አንድሪ ፕራቬድኒክ ዛሬ ናይሮቢ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ ጠይቀዋል።

“ዛሬ የአውሮፓ መፃዒ ዕጣና የዓለም ዕጣ አደጋ ላይ ናቸው። ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በሩሲያ ላይ አውዳሚ ማዕቀቦችን ያለአንዳች መዘግየት ተግባራዊ እንዲያደርግ ዩክሬን ዛሬ ጥሪ ታሰማለች” ብለዋል አምባሳደር ፕራቬድኒክ።

ይሁን እንጂ በሩሲያ ወረራ ላይ የአፍሪካ መንግሥታት ያሉት ምንም ነገር የለም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኬንያ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ ብቻ የሩሲያ ኃይሎች ወደ ዩክሬክ ከመዝለቃቸው ከሦስት ቀናት በፊት ባለፈው ሰኞ የወረራን ሃሳብ አውግዘው ተናግረዋል።

“ኬንያ እንዲህ ዓይነቱን በኃይል ከመገፋፋት የሚመነጭ የገነነ ፍላጎት ትቃወማለች። ከሞቱ ኢምፓየሮች ፍንጥርጣሪዎች የምናደርገውን ማገገም ወደ አዳዲስ የበላይነት ስሜትና ጭቆና መልሶ በማይዘፍቀን ሁኔታ ማጠናቀቅ አለብን” ብለዋል።

አፍሪካ በዩክሬን ወረራ ጉዳይ ዝምታን መርጣለች
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:40 0:00

ዩክሬንና ሩሲያ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ ደቡብ አፍሪካ ትናንት በተናጠል ባወጣችው መግለጫ አሳስባለች።

ሩሲያ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያላትን አቅም ጠንቅቀው የአፍሪካ ሃገሮች ጠንቅቀው እንደሚያውቁ በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የሩሲያ-አፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ ስቲቭን ግሩዝድ ይናገራሉ።

“የአፍሪካ ሃገሮች ሩሲያ በዓለምአቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የምትጫወተውን ሚና ጠንቅቀው ያውቃሉ። የአስተዳደር ጉዳዮች ውስጥ ሳትገባ፣ የሃገሮችን የውስጥ ጉዳዮች ጥያቄ ሳታነሳ ትደግፋቸዋለች። በ2012 ዓ.ም. ሶቺ ላይ 43 የአፍሪካ መሪዎች የተሰበሰቡበት ጉባዔ ተካሂዶ ነበር። ሩሲያ አህጉሩን በማቆላመጥ ታነሳሳለችና ይህ ሃገሮቹ ወቃሽ በመሆናቸው መጠን ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል” ብለዋል።

ሆኖም የአፍሪካ ሃገሮች ድንበሮችን በኃይል የመለዋወጥ ጉዳይ እምብዛም እንደማይጥማቸው የጠቆሙት ግሩዝድ በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ ሃገሮች ነፃ ሲወጡ የተተዉት ከቅኝ ግዛት ድንበሮች ጋር እንደነበር አስታውሰው እነዚያ ድንበሮች የጎሣና የቋንቋ ቡድኖችን የለያዩ ቢሆኑም ሃገሮቹ ሊያከብሯቸው መወሰናቸውን ተናግረዋል። “ካለበለዚያ - አሉ ስቲቭን ግሩዝድ - አጠቃላይ አደጋን መጥራት ነው የሚሆነው።”

ስለዚህ “በሩሲያና በአፍሪካ ሃገሮች መካከል ያለው የፖለቲካ ፍቅር ምናልባት ዝም ሊያስብላቸው ቢችልም አፍሪካዊያኑ በመርኆቻቸው ይፀናሉ። ከእነዚያ መርኆች መካከል ደግሞ የግዛት ጥብቅነትና ሉዓላዊነት አንዱ ነው” ባይ ናቸው ደቡብ አፍሪካዊው ተንታኝ።

የኬንያው አምባሳደር በመንግሥታቱ ድርጅት መድረክ ላይ የተናገሯቸው ቃላት ሃገሪቱ ከመስኮብ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ጫና የመፍጠራቸውን ነገር እንደሚጠራጠሩ የዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ኤክስፐርቱ ኪዚትሶ ሳብላ አመልክተዋል።

“ሩሲያ ይህንን አባባል ከዩናይትድ ስቴትስ ወይም ከሌላ ከማንም እንደተነገሩ የተለመዱ ቃላት ሁሉ ቆጥራ ጣል ታደርገዋለች። ማድረግ የሚፈልጉትን፣ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑበትን በማድረግ ይቀጥላሉ። የኬንያ-ሩሲያ ግንኙነቶችን ግን ይጎዳሉ ብዬ አላስብም” ብለዋል።

ሩሲያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተፅዕኖዋን ቡርኪና ፋሶ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ማሊና ሊብያ ውስጥ አበርትታለች። አንዳንድ መንግሥታት ደግሞ አማፂ ቡድኖችን ለመዋጋት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ተጠቅመዋል።

እንደዚያ ቅጥረኞች በሲቪሎች ላይ የተስፋፉ ጥቃቶችን ይፈፅማሉ የሚሉ ክሦች ይሰሙባቸዋል። የሩሲያ መንግሥት ግን ከቅጥረኞቹ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ይናገራል።

XS
SM
MD
LG