ካለፈው አመት ወዲህ ከሃገራቸው ከተሰደዱት 176,000 የመናውያን ወደ ግማሽ የሚጠጉት ወደ አፍሪቃ ቀንድ አከባቢ እንዳመሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰደተኞች አገልግሎት ገልጿል። ብዙዎቹ ወደ ሃገሮቻቸው የሚመለሱ አፍሪቃውያን ሲሆኑ 26,000 የሚሆኑት ግን መድረሻ የሌላቸው የመናውያን ናቸው።
ዋሲም ሰይድ መሐመድ ዐደን የሚገኘው መኖርያ ቤታቸው በሑቲ አማጽያን ከተመታ በኋላ ባለፈው የካቲት ወር ከባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው ጋር ወደ ሶማሊላንድ ተሰደዱ። መኖርያ ቤታቸው በተመታበት ወቅት እንደ አጋጣሚ ሆኖ መላው ቤተሰብ እቤት ውስጥ አልነበረም። ይሁንና መሐመድ ቤተሰባቸውን ይዘው ከበባ ስር ወዳልሆነችውና የየመን ፓስፖርትን ማለትም የይለፍ ሰነድን ከሚቀበሉት አገሮች አንዷ ወደ ሆነችው ሶማሊላንድ ተሰደዱ።
“የኑሮ ውድነት የሌለባት ሀገር እቺ ብቻ ናት። በዛም ላይ የጸጥታው ሁኔታ ጥሩ ነው። ከህዝቡ ጋር ተዋህደን መኖር እንችላለን” ይላሉ መሐመድ። የስራ እድልም አግኝተዋል። የአጎታቸው ወዳጅ በሆነው ሶርያዊ ዳቦ ቤት ተቀጥረው ይሰራሉ።
“እዚህ ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው። ይሁንና የሚያስፈልጉኝ ቁሳቁስና ድጋፍ አላገኘሁም። ወደ ሌላ ሀገር መሄድ እፈልጋለሁ። ግን ካባድ ነው። ባለቤቴንና ሁለት ሴት ልጆቼን ይዤ በባህር ሊገጥመን የሚችለውን አደጋ መጋፈጥ አልፈልግም። በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮፓ ወይም ሌላ ቦታ የመሄድ እድል ባገኝ እሄዳለሁ።”ብለዋል።
ለየመን ስደተኞች ያለው እድል የተወሰነ ነው። ብዙዎቹ ለህገ-ወጥ አሸጋጋሪዎች የሚከፍሉት ገንዘብ የላቸውም። በዐደን ባህረ-ሰላጤ በኩል ግብጽ ሄደው ወደ ሜዲትራንያን ባህር ለመድረስም ገንዘብ ያስፈልጋል። እንደዛም ሆኖ ወደ አውሮፓም ሆነ ወደ ቱርክ ለመጓዝ ብዙዎቹ ቪዛ ለማግኘት አይችሉም።
ሶማሊላንድ የተረጋጋ ሁኔታና መልካም የአስተናጋጅነት መንፈስ ቢኖራትም ደሀ ግዛት መሆንዋ አልቀረም። የስራ አጥነት ብዛትም ከፍተኛ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰተኞች አገልግሎት እንደሚለው ከየመን ሶማሊላንድ ከገቡት 10,000 ሰዎች 1,900 ዎቹ የመናውያን ናቸው። ሶማሊላንድ ውስጥ የስደተኞች ሰፈር የለም። የግዛቲቱ መንግስት የስደተኞች ሰፈር መግንባቱን አይቃወምም። የሰደተኞቹ አገልግሎት ግን ስደተኞቹ መጠለያ ለመገንባት የሚያስፈልግ ያህል ብዛት እንደሌላቸው አስገንዝቧል።
ሶማሊላንድ ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ እአአ በ 1991 ዓ.ም ከሶማልያ ተገንጥላ የራስዋን አስተዳደር መሰርታለች። ስለሆነም የሶማሊላንድ ህዝብ የስደተኝነትን ተመክሮ ጠንቅቆ ያውቃል። ይሁንና ይዞታው ውሱን ነው። የሶማሊላንድ መልሶ የማስፈር ሚኒስትር ዐሊ ሰይድ ራይጋል ያብራራሉ።“ስደተኞቹ ከሶማሊላንድ ነዋሪዎች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። ምክኒያቱም የግዛቲቱ ህዝብም በቂ የስራ እድል የለውም። ስለሆነም ማንኛውም ክህሎት ያለው ሰው እዚህ ሊሰራ ይችላል። ልንረዳቸው እየሞከርን ነው።”ብለዋል።
ስደተኞቹ ሶማሊላንድ ሲገቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች አገልግሎት ምግብ፣ የህክምና አገልግሎትና እያንዳንዳቸው $100 ዶላር ገደማ በመስጠት ይቀበሏቸዋል። ከፈለጉም በሶማልያ ውስጥ የመጓጓዣ አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ። ይሁንና ለአንዳንዶቹ ይህ በቂ አይደለም። ጂሀን ዐሊ የተባለች የመናዊት ሰደተኛ ወደ ሰለጠነ ሀገር መሄድ እፈልጋልሁ ትላለች።
“ወደ ሰለጠነ ሃገር መሄድ እፈልጋልሁ። በገንዘብ ራሴን መቻል እፈልጋለሁ። ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እፈልጋለሁ። ጥሩ ህይወት እንዲኖረኝ ነው የምመኘው። እዚህ ግን ኑሮ አይደለም።”ብላለች።
ለአሁኑ ግን እዚያው ሶማሊላንድ ባለው ሁኔታ ከመኖር በስተቀር ሌላ አማራጭ የላቸውም።
የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዘጋቢ ጂል ክሬግ ከሀርጌሳ ሶማሊላንድ የላከችልንን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ አቅርባዋለች፣ ከድምጽ ፋይሉ ያድምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5