ዩናይትድ ስቴትስ የመን ውስጥ በሚገኝ አንድ የአል-ቃይዳ ማሠልጠኛ ካምፕ ላይ ባካሄደችው የአየር ድብደባ፥ ብዛት ያላቸው አሸባሪዎች ተገድለዋል ሲል ፔንተገን ማለትም የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ ትላንት አስታውቋል።
ጥቃቱ በአረቡ-ሠላጤ የአልቃይዳ እንቅስቃሴ ላይ ከባድ በትር በማሳረፍ፥ የመንን እንደ መጠለያ በመጠቀም በዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ስጋት ያስወግዳል ሲልም አስረድቷል። የፔንታገን ቃል አቀባይ ቲተር ኩክ (Petyer Cook) አክለውም፥ የተወሰደው እርምጃ የሚያሳየው፥ አል-ቃይዳን ለማሸነፍና ቡድኑ በየትም ሥፍራ መጠለያ እንዳያገኝ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ብለዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ከ 70 በላይ አሸባሪዎች ካምፑ ውስጥ በሥልጠና ላይ እንደነበሩና፥ ያየር ጥቃቱ በትክክል ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ለማወቅ፥ ባለሞያዎች አሁንም እአመረመሩ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ጨምረው አስረድተዋል። ከወዲሁ የተገኙ ውጤቶች ግን በደርዘኖች የሚቆጠሩ የአል-ቃይዳ አባላት መገደላቸውን ያሳያሉ ሲሉም አብራርተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፥ ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ካላቸው አሸባሪ ቡድኖች ውስጥ፥ በአረቡ ሠላጤ የየመኑ ቅርንጫፍ፥ ከሁሉም አደገኛው ነው ይላሉ።
ይህ ቡድን በዚያች ሀገር የሚካሄደውን ውጊያ፥ ትርምስና የፖለቲካ ቀውስ በመጠቀም፥ መሬት ሲመቀራመትና የሽብር ጥቃት ሲያደርስ ይታያል።