ለአንድ ዓመት በዘለቀው የየመን የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ አንድ ሚሊየን የሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች ሁኔታ እያሳሰባቸው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እያሳወቁ ነው፡፡
ሳዑዲ አረቢያ የአየር ድብደባ ከጀመረች ወዲህ ባለው ጊዜ ከሦሰት ሺህ በላይ ሲቪሎች መገደላቸውንና ወደ ስድስት ሺህ መቁሰላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል፡፡
ቁጥሮቹ የሚያሳዩት ካለፈው ዓመት መጋቢት 17 አንስቶ እየተካሄዱ ባሉት ድብደባዎች በሲቪሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እንጂ በታጣቂዎቹ ወገኖች በራሣቸው መካከል ግን ምን ያህል ሰው እንደተገደለና ምን ያህል እንደቆሰለ እንደማይናገሩ ተዘግቧል፡፡
ባለፈው የአውሮፓ ዓመት ውስጥ ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ በጦርነት ወደምትታመሰው የመን ከዘጠና ሁለት ሚሊየን በላይ ሰው መግባቱን ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት - አይኦኤም አስታውቋል፡፡
የመን ውስጥ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ለሚባሉ ቁጥራቸው 13.6 ሚሊየን ሰዎች ድጋፍ ለማድረስ 1.2 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢያስታውቅም አሁን በካዝናው የሚገኘው ግን ሁለት ከመቶው ብቻ መሆኑን ገልጿል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡