የተ.መ.ድ. የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ ተካሄደ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ /ፎቶ - ገልሞ ዳዊት/

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ የሚተች ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ ላይ ተካሄደ።

በጉባዔው ላይ እስካሁን የቀረቡት ሰነዶችና ጥናቶች የዓለማችን የተፈጥሮ አካባቢ ደኅንነት አደጋ ላይ መሆኑን ያሳያሉ።

በተፈጥሮ አካባቢ ብክለት ምክንያትና መቆራቆዝ በእስያና በአፍሪካ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰው ለምግብና ለመጠጥ ውኃ እጥረት መዳረጉን ጉባዔው ጥናታዊ ማስረጃዎችን አቅርቦ ተነጋግሯል።

በተለይ የከተሞች በብዛት መበከል በየዓመቱ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰው ለህልፈት እንዲዳረጉ እንደሚያደርግ በጉባዔው ላይ የወጡ ጥናታዊ ፅሁፎችን የያዘ መፅሔት ያስረዳል።

ብክለቱን እያስከተሉ ካሉት ጠንቆች መካከል ኃላፊነት የጎደለው የማገዶ አጠቃቀምና ሰደድ እሳት መሆናቸውንም ይህ ጥናት በስፋት አስቀምጧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ /ፎቶ - ገልሞ ዳዊት/

ሮብ ዲጆንግ በተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ጉባዔ የትራንስፖርትና ጎጂ ውጤቶቹ ተከታታይ ክፍል አስተባባሪ ናቸው።

በጉባዔው ላይ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን ባቀረቡበት ወቅት ተጨባጩ ሁኔታ ብዙ መሠራት እንዳለበት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ባለሥልጣን - ኢጋድ አባል ሃገሮች በካይ በሆኑ የተሽከርካሪዎች ውጤቶች ዙሪያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ የህግ ማዕቀፍ ያወጡ ሲሆን የተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች ይንን ተሞክሮ ቢጠቀሙ የከተሞቻቸውን የአየር ጥራት ደረጃን ማሻሻል እንደሚችሉ ጥናቱ ያብራራል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ /ፎቶ - ገልሞ ዳዊት/

የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው የብክለት ደረጃ ስሟ አብዝታ በመበከሏ ሲጠራ የቆየችው የቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአየር ብክለት ቁጥጥር አሠራር በመተግበሯ ከዕለተዕለት ለውጥ እያሳየች መሆኗን የቻይና ልዑክ ፕሮፌሰር ሂ ኬብር በጉባዔው ላይ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉባዔ በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ /ፎቶ -ገልሞ ዳዊት/

ይሁን እንጂ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶች በወጡ ቁጥር የዓለማችን አየር ለብክለት ስለሚጋለጥ አሁን ያለውን የተሽከርካሪዎችና የሌሎች በካይ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ቁጥጥር መስፋት እንዳለበት በዩናትድ ስቴትስ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳንኤል ሬይፍሲይንደር ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራርያ አስረድተዋል።

እንደ የእንግልዙ ኢንዲፐንደንት( The Independent) ጋዜጣ ዘገባ የህንድ ከተሞች በአየር ብክለት በቀዳሚነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በተለይ ኒው ዴልሂ ከተማ ከመጠን በላይ በመበከሉ ብዙ ነዋሪዎችዋ በዚሁ ምክንያት እየሞቱ መሆኑንም ዘገባው ይጠቁማል። በህንድ ለሁለት የአዝመራ ጊዜ ዝናብ ባለመጣሉም ከ300 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ ለውኃ እጥረት ተጋልጠዋል።

ክሪሽና ኩማር ዘ ሂንዱ (The Hindu) ለተባለ የህንድ ጋዜጣ የሚሠራ ጋዜጠኛ ነው። በእውን እያየንና በሪፖርቶች እየሰማን ያለነው ብዙም የሚጣጣም ስላልሆነ የተለያዩ ሃገሮች ፖሊሲ አስፈፃሚዎች ዕቅዶችን በፍጥነት ወደ መተግበር መግባት እንዳለባቸው ይመክራል።

የአፍሪካና የእስያ ሃገሮች በንፁህ አየር፣ በዝናብ እጥረጥና በድርቅ እየተጎዱ በመሆናቸው መሪዎቻቸው ለእነዚህ የብዙ ሰው ህይወት ማለፍ ምክንያት እየሆኑ ላሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የተፈጥሮ አካባቢ ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር አሺም ስታይነር በጉባዔው ተናግረዋል።

በተለይ አፍሪካ ላይ በደረሰው ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰው ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት ተጋልጧል።

ይህንን መሰል ችግር በተደጋጋሚ እንዳይከሰት የአካባቢ አየር የሚያስከትሉትን የተሽከርካሪዎች ጋዝ ልቀትን የመሳሰሉ ችግሮችን መቆጣጠር ተገቢ መሆኑን ሚስተር ስታይነር ያስረዳሉ።

ጉባዔው በሐሙስ ውሎው በዱር እንስሳት ላይ እየተፈፀመ ስላለው ወንጀል እየተወያየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህገወጥ አደን የተከሰሱ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በተለይ የአፍሪካና የእሥያ መንግሥታት መሪዎች በስፋትና በብርታት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ገልሞ ዳዊት ከናይሮቢ አጠናቅሮ የላከውን ዘገባ ከድምጽ ፋይሉ ያድምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

የተ.መ.ድ. የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሁለተኛ ጉባዔ በናይሮቢ ተካሄደ