ጆሃንስበርግ —
በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ለድርቅ አመጣሽ ችግር ይጋለጣል የተባለው ሰው ቁጥር ይሆናል ተብሎ ቀድሞ ከተገመተው ይበልጣል ሲሉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ዓለምአቀፍ ፌደሬሽን ዋና ፀሐፊ ኤልሃጅ አህሲ አስታውቀዋል።
ሊደርስ የሚረባው የአጣዳፊ እርዳታ መጠን በቂ እንዳልሆነና ችግሩን የመሸከም አቅም ወይም የተለማጭነቱና የመሠረተ-ልማት ችግሮችም ትኩረትና የተግባር እርምጃ የሚፈልጉ መሆናቸውን ሚስተር አህሲ አሳስበዋል።
ይህ የደቡባዊ አፍሪካ የበረታ ድርቅ ከመርገቡ በፊት እንዲያውም እየተባባሰ እንደሚሄድ መስክ ላይ ያሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች በብርቱ እየጎተጎቱ ናቸው።
በኤል ኒኞ ምክንያት የተከሰተው ድርቅና ተከትሎም የሚታየው አደገኛ ጎርፍ ደቡባዊ አፍሪካን ለሰፋ ጉዳት ዳርጎ የተጎጂውና የዕለት እርዳታ የሚፈልገው ሰው ቁጥር ከ22 ወደ 49 ሚሊየንና ከዚያ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ሚስተር አህሲ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ዓለምአቀፍ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊው ሰሞኑን ማላዊና ዚምባብዌ ውስጥ ድርቁ አብዝቶ ያጠቃቸውን አካባቢዎች ተመልክተዋል።
አኒታ ፓወል የላከችውን ዘገባ ሰሎሞን አባተ አቅርቦታል፣ ከድም ፋይሉ ያድምጡ።