የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተመሰረተበትን 80 ዓመት ማክበር የጀመረው፣ 80 ዓመቱን ከደፈነበት ካለፈው ዓመት ከሚያዝያ 30 ቀን ጀምሮ ነው። ማኅበሩ በዘረጋው እቅድ መሰረት በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የምስረታውን 80 ዓመት ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ዛሬ የነዚህ ዝግጅቶችን ማጠናቀቂያ የሆነውን መሰናድኦ አድርጎ፣ የኢትዮጵያው ፕረዚደንትና የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዝግጅቱን መርቀው ከፍተዋል።
ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የዘንድሮን የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ በአል ልዩ የሚያደርገው መአለም በኩል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአገራችን በተከሰተው ድርቅ ከ10 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችንን ከችግር ለመታደግ ርብርብ የምናደርግበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ አላማ የሌላቸው ከደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ድምበር ጥሰው የመጡ ኃይሎች በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 208 ወገኖቻችን ላይ የፈጸሙትን ኢሰብአዊ ጭፍጨፋና የ108 ህጻናት ታፍኖ መወሰድ በኃዘን የምናስብበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።
ዛሬ የኤግዚብሽኑ እና የባዛር ዝግጅቶቹ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ከዝግጅቱ የተገኘው ገቢ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ይውላል። መለስካቸው አመሃ ዝግጅቱን ተከታትሏል፣ የላከውን ዘገባ ከድምጽ ፋይልይ ያድምጡ።