በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በካርቱም ችላ የተባለው የተኩስ አቁም


በካርቱም ችላ የተባለው የተኩስ አቁም
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:45 0:00

በካርቱም ችላ የተባለው የተኩስ አቁም

►እስከ አሁን የሟቾች ቁጥር 270 ደርሷል

በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት፣ በሱዳን የጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ልዩ ኃይሎች መካከል የተደረሰው፣ “የ24 ሰዓት ተኩስ ማቆም ስምምነት” መክሸፉን ተከትሎ፣ በሱዳን ዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ የሚደረገው ጦርነት፣ ረቡዕ ዕለትም ቀጥሎ ውሏል፡፡

በግጭቱ ምክንያት፣ በርካታ ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጪ መኾናቸውንና መሥሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸውን፣ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይፋ ያደረጉ ሲኾን፣ በርካታ ዝርፊያዎች እና ጥቃቶች መፈጸማቸውን፣ እንዲሁም አገልግሎት መስጠት ባላቋረጡ ዳቦ ቤቶችም፣ ረጅም ወረፋዎች መታየታቸው ተዘግቧል።

በማዕከላዊ ካርቱም፣ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና የከተማውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ፣ ተዋጊዎች ያጥለቀለቁት ሲኾን፣ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው ፍንዳታዎች እና ተከታታይ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ውሏል።

በርካታ የካርቱም ነዋሪዎችን ከቤታቸው እንዳይንቀሳቀሱ ያገደውን የአራት ቀናት ጦርነት ለማስቆም፥ በአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ መሪዎች ግፊት፣ ማክሰኞ ጠዋት የተደረሰውን የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማክበር፣ የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ወይም በእንግሊዝኛው ምሕጻረ ቃሉ - አርኤስኤፍ ተብሎ የሚጠራው ኃይል አዛዥ የኾኑት ጀነራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ፣ ሕዝባዊ መግለጫ ቢሰጡም፣ ጦርነቱ ግን ማክሰኞ ምሽቱን ቀጥሎ አድሯል።

ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን፣ ቢያንስ 270 ሰዎች ሲሞቱ፣ 2ሺሕ 600 ደግሞ መቁሰላቸውን፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የሱዳንን የጤና ሚኒስትር ጠቅሶ አስታውቋል።

ሮይተርስ ያነጋገራት፣ በካርቱም ምሥራቃዊ ዳርቻ የምትኖር ግለሰብ፣ ባለፈው ማክሰኞ፣ ከቤቷ አቅራቢያ ከተካሔደው የአየር ድብደባ እና ተኩስ በኋላ፣ ዛሬ ረቡዕ ማለዳም፣ ከባድ ውጊያ መቀጠሉን ገልጻለች፡፡ “መተኛት አልቻልንም። ጸጥታ የነበረበት ብቸኛው ሰዓት፣ ከለሊቱ 9 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 የነበረው ጊዜ ብቻ ነው፤” በማለት አስከፊ እየኾነ መምጣቱን አስረድታለች፡፡

ከካርቱም ሸሽተው ለመሰደድ የሚሞክሩ ሰዎች በአዎቶቢስ መሳፈሪያ ጣቢያ ተሰብስበው ይታያሉ
ከካርቱም ሸሽተው ለመሰደድ የሚሞክሩ ሰዎች በአዎቶቢስ መሳፈሪያ ጣቢያ ተሰብስበው ይታያሉ

በሰሜን ካርቱም፣ ባሕሪ ወረዳ የሚገኘው የአሕመድ ቃሲም የሕፃናት ሆስፒታል፣ ሜዲካል ዲሬክተር መሐመድ አል-ሙስታፋም እንዲሁ፣ ስለ ኹኔታው ለአሶሽዬትድ ፕሬስ ሲያስረዱ፣ “ሆስፒታሉ እስከ ቅዳሜ ጠዋት አምስት ሰዓት ድረስ ሥራውን ቀጥሎ ነበር። በሆስፒታሉ የነበሩት 21 ዶክተሮች እና 38 ነርሶች ናቸው። ሁከቱ እና ውጥረቱ እየተባባሰ ሲሔድ ግን፣ ዶክተሮቹ፣ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ካሉት በስተቀር ሌሎች ታካሚዎችን ማስወጣት ነበረባቸው። ብዙ እጥረት እየታየ ነው፤ ሐኪሞች እንኳን ለቀው ሔደው፣ ሆስፒታሉ ውስጥ አንድም ሰው የለም፤” ብለዋል።

ተኩስ የማቆም ስምምነቱ ተደርሶ የነበረው፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ከቡርሃንና ዳጋሎ ጋራ በስልክ ከተነጋገሩና ጦርነቱን በአስቸኳይ በማቆም ሰብአዊ ርዳታ ይደርስ ዘንድ እንዲፈቅዱ ከአሳሰቧቸው በኋላ ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም፣ ብሊንከን፥ ቡርሃንና ዳጋሎ በሱዳን የሚገኘው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ “ደኅንነቱ የተጠበቀ መኾኑን የማረጋገጥ” እና “የሲቪሎች፣ የዲፕሎማቲክ ሠራተኞች እና ሰብአዊ ሠራተኞች ደኅንነት የማስጠበቅ” ሓላፊነት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ገልጿል።

ብሊንከን፣ ለሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኞች ያቀረቡት ጥሪ፣ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሰላም እንዲሰፍን ከሚደረጉት ዓለም አቀፍ ጥረቶች መሀከል አንዱ ሲኾን፣ በጃፓን፣ ካሮዛዋ ከተማ በተካሔደው የቡድን ሰባት የበለጸጉ ሀገራት ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአወጡት መግለጫ ጦርነቱን አውግዘዋል።

እ.አ.አ እሁድ ሚያዚያ 19፣ 2023 ፣ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ጭስ ይታያል
እ.አ.አ እሁድ ሚያዚያ 19፣ 2023 ፣ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ጭስ ይታያል

የተኩስ ማቆም ስምምነቱን መክሸፍ ተከትሎ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ የሱዳንን ግጭት የሚከታተል ልዩ ኃይለ ግብር ማቋቋሙን፣ ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ አስታውቀዋል።

ቃል አቀባዩ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳረጋገጡት፣ “የሱዳን ወታደራዊ ግጭት ኃይለ ግብር፥ ከሱዳን ጋራ የተያያዘውን የመሥሪያ ቤቱን ዕቅድ፣ አስተዳደር እና የሎጂስቲክስ ጉዳዮች ይከታተላል። ዩናይትድ ስቴትስ፣ በሱዳን የጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች(አርኤስኤፍ) መካከል የተፈጠረውን ሁከት፣ በከፍተኛ ኹኔታ ታወግዛለች፤” ያሉት ፕራይስ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ፣ “የሱዳናውያንን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥልና የሱዳንን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክም ነው፤” ብለዋል።

የሱዳኑ ውጊያ እንዲቆም ተማፅኖው ቀጥሏል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:38 0:00

ካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ በአወጣው የጸጥታ ማስጠንቀቂያ፣ እስከ አሁን በሱዳኑ ግጭት ሕይወታቸው ያለፈ ወይም ጉዳት የደረሰባቸው የአሜሪካ ዜጎች ስለመኖራቸው፣ መረጃ እንዳልደረሰው ገልጾ፣ በካርቱም ባለው የጸጥታ ችግር እና በአውሮፕላን ማረፊያው መዘጋት ምክንያት፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ ዜጎችን የማስወጣት ዕቅድ እንደሌለው አስታውቀዋል። ኾኖም መግለጫው አክሎ፣ “በሱዳን ያሉ የአሜሪካ ዜጎች እንደዚኽ ባለ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ፣ የራሳቸውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፤” ሲል አሳስቧል። ሌላ ተጨማሪ መረጃ እስከሚወጣም፣ የአሜሪካ ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ አስጠንቅቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሱዳን ያለው ኹኔታ አሳሳቢ መኾኑንና በሱዳን የጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መካከል እየተደረገ ያለው፣ ጦርነት በርካቶችን እንዳይንቀሳቀሱና መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ማገዱን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል።

የቡድኑ የሥራ እንቅስቃሴ ሥራ አስኪያጅ አብደላ ሑሴን አብደላ፣ በሰሜን ዳርፉር ኤል ፋሸር ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ የተመለከቱትን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሲያስረዱ፥ “ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እየሆነ ባለው ነገር ኤል ፋሸር ውስጥ ያለው ሁኔታ ውጥረት የበዛበት ነው፤” ያሉ ሲኾን፣ "ኅብረተሰቡ በግጭቱ መካከል አጣብቂኝ ገብቷል። በርካታ ሰዎች ቆስለዋል። ሆስፒታሎቹንና ድንበር የለሽ የሕክምና ቡድኑን በተመለከተ፣ እስከ ትላንትና ድረስ፣ 183 የቆሰሉ ሰዎችን ተቀብለናል። አብዛኞቹ ሕፃናትን ያካተቱ ሲቪሎች ሲኾኑ፣ ኹሉም መደበኛ ኑሯቸውን በሚኖሩበት ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ናቸው፤” ብለዋል።

አብደላ አክለው፣ ኤል ፋሸር በአካባቢው ብቸኛ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሆስፒታል መኾኑን ገልጸው፣ ወደ ሆስፒታሉ እየመጡ ያሉት በግጭቱ የቆሰሉ ብቻ አለመኾናቸውንም አመልክተዋል።

በሱዳን መዲና፣ ካርቱም የደረሰው ጥቃት ካስከተለው የእሳት ቃጠሎ የተነሳ ጭስ ወደ ላይ ሲወጣ ይታያል- እሁድ፣ ሚያዚያ 16፣ 2023
በሱዳን መዲና፣ ካርቱም የደረሰው ጥቃት ካስከተለው የእሳት ቃጠሎ የተነሳ ጭስ ወደ ላይ ሲወጣ ይታያል- እሁድ፣ ሚያዚያ 16፣ 2023

“ዛሬ በኤል-ፋሸር አገልግሎት እየሰጠ ያለው ብቸኛው ሆስፒታል፣ በድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ድጋፍ የሚደረግለት ይህ ሆስፒታል ብቻ ነው። በተቻለን ዐቅም ኅብረተሰቡን ለመርዳት እየሞከርን ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣው የቆሰለ ሰው ብቻ አይደለም። ሌሎችም ለምሳሌ፥ ልጅ የሚወልዱ እናቶች እና ሌላ ሕመም ያለባቸውና ሌሎች ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ባለመኾኑ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ያልቻሉ ሰዎችም ይመጣሉ።”

በሱዳን ዋና ከተማ እየተካሔደ ባለውና አምስተኛ ቀኑን በአስቆጠረው ከፍተኛ ውጊያ ምክንያት፣ በርካታ ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጪ መኾናቸውን፣ የሱዳን የሕክምና ባለሞያዎች ገልጸዋል። በካርቱም የሚገኙ እንደ አል-ሻብ፣ ኢብን ሲና፣ ባሽር፣ አል-ቱርኪ እና የኩላሊት ሕመም ማዕከል የመሳሰሉ በርካታ ሆስፒታሎች፣ የሚታከሙ ሕመምተኞች እና ሠራተኞች ሙሉ ለሙሉ እንዲወጡ የተደረጉ ሲኾን፣ እንደ ፋዲል፣ አል-ባራሃ እና ሐጂ አል-ሳፊ የመሳሰሉቱ ደግሞ፣ ከአገልግሎት ውጪ ኾነዋል። ሱዳናውያን፥ የጤና ተቋማቱ መዘጋት፣ ሰብአዊ ወንጀል እንደኾነ ይገልጻሉ።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው፣ የሱዳን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሃይታም ኢብራሂም በበኩላቸው፣ በጎ ፈቃደኞቻችቸው በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን ለማግኘት መቸገራቸውን አስረድተዋል። በየቦታው በወደቁት አስከሬኖች ምክንያት፣ ካርቱም አደገኛ ሥፍራ ከመኾኗም በፊት፣ ሁለቱ ተዋጊ ወገኖች ቢያንስ የሞቱትን ሰዎች ይቀበሩ ዘንድ እንዲፈቅዱም ጠይቀዋል።

“ኹኔታው ተስፋ ሰጪ አይደለም፤” ያሉት ኢብራሂም፣ “በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ አፋጣኝ ኦክስጂንና ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አሉ። ይህ ለሁለቱ ተዋጊ ወገኖች፣ የሕክምና ርዳታ ከአቅርቦች ማከማቻ ቦታዎች ወደ ሆስፒታሎች እንዲጓጓዙ እንዲፈቅዱ የሚተላለፍ መልዕክት ነው፤” ብለዋል።

በሱዳን የጦር ሰራዊት እና ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ መካከል በካርቱም እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የተፈጠረው ጭስ ከህንፃዎቹ በላይ ይታያል
በሱዳን የጦር ሰራዊት እና ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ መካከል በካርቱም እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የተፈጠረው ጭስ ከህንፃዎቹ በላይ ይታያል

ሌላው፣ በካርቱም ነዋሪ የኾነው ሐሰን ኢብራሂም፣ ለመዘጋት ከተገደዱት የጤና ተቋማት አንዱ በኾነው፥ የካርቱም ነርሶች ማሠልጠኛ ሆስፒታል፣ በነርስነት ያገለግላል፡፡ “ካርቱም የሚገኘው ዋናው የካርቱም ነርሶች ማሠልጠኛ ሆስፒታል፣ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። እዚያ የሚሠሩ የጤና ባለሞያዎች፣ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሌሎች ደግሞ ተጎድተዋል። በካርቱም ዩኒቨርሲቲ የሚማሩና ላለፉት አራት ቀናት ከዚያ መውጣት ያልቻሉ ተማሪዎችም አሉን። ምንም የሚበሉት የላቸውም፤” በማለት፣ ሰኞ ጠዋት በከተማዋ እንብርት የነበረው ከባድ የቦምብ ድብደባ፣ በሆስፒታሉ ሥራ ለመቀጠል አዳጋች እንዳደረገው ይገልጻል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴም እንዲሁ፣ ዛሬ ማምሻውን በአወጣው መግለጫ፣ በሱዳን ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ አፋጣኝ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደረግ በድጋሚ ጠይቋል። በመዲናዋ የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ አስጊ በኾነ ኹኔታ፣ ከፍተኛ የሕክምና ዕቃዎች አቅርቦት እንዳጋጠማቸው ገልጾ፣ በውኃ እና በኃይል አቅርቦቶች ላይ የደረሰው ጉዳት፥ የሕክምና ተቋማት፣ ኤሌክትሪክ እና ንጹሕ ውኃ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፤ ብሏል።

መግለጫው፣ የሕግ እና ሥርዓት መፈራርስ ይታይባቸዋል፤ ባላቸው የዳርፉር አካባቢዎች፣ የተቋሙ ቢሮ መዘረፉንና አንድ አሽከርካሪው መወሰዱን አመልክቷል፡፡ የቀይ መስቀል የአፍሪካ ዲሬክተር ፓትሪክ ዩሱፍ፣ “በንጹሐን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት እና በካርቱም ጎዳናዎች ላይ አስከሬኖች በየቦታው መውደቃቸውን መስማት እጅግ አሳዛኝ ነው፤” ማለታቸውን አክሎ አስታውቋል።

የሱዳን ግጭት መነሻዎች እና ተከታይ ቢኾኖች በምሁሩ አንደበት
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:00 0:00

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአውሮፓ ኅብረት ሱዳን በሚገኝ አባሉ ላይ ጥቃት መድረሱን ዛሬ አረጋግጧል። የአውሮፓ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ናቢላ ማስራሊ፣ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ኮሚሽኑ በጸጥታው ኹኔታ መደናገጡን ጠቅሰው፣ በአባላቸው ላይ የደረሰውን ጥቃት ሀገራት፣ በቪየና ጉባኤ ያደረጉትን ስምምነት የሚጥስ ነው፤ ብለዋል።

“የኾነው ነገር፥ የጄኔቫ ጉባኤንም ኾነ በቪየና ጉባኤ የተደረገውን ስምምነት የሚጥስ ነው። ይህ ያሳስበናል። ኹኔታውን በጥንቃቄ መከታተላችንን እንቀጥላለን። ሰዎችን የማስወጣትን ጉዳይ በተመለከተ፣ የሠራተኞቻችን ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። እስከ አሁን ድረስ ሁሉም ሠራተኞቻችን፣ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው። የአውሮፓ ኅብረት ልኡካን ቡድን፣ እስከ አሁን እንዲወጡ አልተደረገም። አሁን እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት፣ የደኅንነት ርምጃዎች እየተገመገሙ ነው።”

የኤሌክትሪክ እና የውኃ አገልግሎት የተቋረጠው፣ በአብዛኛው የመዲናዋ ካርቱም ክፍል ቢኾንም፣ ግጭቱ አጎራባቾቹን ኦምዱርማንና ባሕሪ ከተሞችንም የጎዳ ሲኾን፣ ከተሞቹን የሚያገናኙት ድልድዮች በብረት ለበስ መኪናዎች ተዘግተዋል።

ግጭቱ እንዲቆም፥ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአረብ ሊግ እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት(ኢጋድ)ን ጨምሮ፣ ከአፍሪካ እና ከዓለም ዙሪያ የሚደረገው ጥሪ እንደቀጠለ ነው፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኦማር ጉሌ፣ አስቸኳይ የተኩስ ማቋም ስምምነት እንዲደረግ ለማደራደር ወደ ካርቱም ያቀናሉ።

የሱዳን፣ ሁለቱ ከፍተኛ ጄነራሎች ግን፣ እስከ አሁን ለመደራደር ፈቃደኛ መኾናቸውን አላሳወቁም፡፡ ይልቁንም፣ አንዱ ሌላውን እጅ እንዲሰጥ መጠይቃቸውን አልያም ፍጹም ድምሰሳውን እንዲጠብቅ መፎከራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።

XS
SM
MD
LG