በሱዳን፣ በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ፣ ከተጀመረ ጀምሮ ፤ በተባራሪ ጥይት የተገደሉና የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን እንደሚገኙ ካርቱም ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ተናገሩ።
የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸው ሦስት ስደተኞች ቤታቸውን ዘግተው በፍርሃት እና በጭንቀት ውስጥ መኾናቸውን ገልፀው፤ የዓለም መንግሥታት ግጭቱን ለማስቆም ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሱዳን የኦሮሞ ማኅበረሰብ የጅረት ቅርንጫፍ ሓላፊ አቶ እያሱ አዶላ ሟቾቹ በስም እና በፎቶ ተለይተው መረጃ እንደደረሳቸው ገልፀው፤ ማምሻውንም የጦር መሳሪያ ተኩስ ድምፅ እንዳልተቋረጠ ተናግረዋል።
ዛሬ እኩለ ቀን ላይም በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት መንግሥት ሲቪሎች ከዋና ከተማዋ እንዲለቁ መልዕክት ቢያስተላልፍም፣ የጸጥታ ሁኔታው አስጊ በመኾኑ ማንም እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው ስደተኞች አስታውቀዋል።
ስደተኞቹ እስካሁን ድረስ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልም ኾነ ከምንግሥታቱ ድርጀት የሰሙት ነገር አለመኖሩን ገልጸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊቱን እንዲያዞርላቸው ተማጽነዋል።