በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳኑ ውጊያ እንዲቆም ተማፅኖው ቀጥሏል


የሱዳኑ ውጊያ እንዲቆም ተማፅኖው ቀጥሏል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:38 0:00

የሱዳኑ ውጊያ እንዲቆም ተማፅኖው ቀጥሏል

በሱዳን ዋና ከተማ በካርቱም፣ እየተካሔደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የሚቀርበው ዓለም አቀፍ ጥሪ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይኹን እንጂ፣ ተፋላሚ ኃይላቱ መሣሪያዎቻቸውን እንዲያወርዱ ሌሎች አገሮች የሚያደርጉት የማግባባት ጥረት ይሳካላቸዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም እንዳለ ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት እና የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት፣ ሰላም ይሰፍን ዘንድ፣ ዋሽንግተን በቀጣናው ያላትን ተጽእኖ የመፍጠር ውስን አቅም ተጠቅመው እንደሚሞክሩ አመልክተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሱዳንን ቀውስ የሚከታተል አንድ ልዩ ኃይለ ግብር ማቋቋሙን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል፡፡ በሱዳን ዋና ከተማ፣ የበላይነትን ለመያዝ በሚፋለሙ ሁለት ወገኖች መካከል፣ ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው ውጊያ የቀጠለ ሲሆን፣ በውጊያው መሀል አጣብቂ ውስጥ ገብተው መውጫ ያጡ ሰላማዊ ሰዎች፣ ለአስከፊ አደጋ መጋለጣቸው ተመልክቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ለሱዳን ጦር ኃይሎች እና ለፈጥኖ ደራሹ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መሪዎች፣ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ጃፓን ውስጥ፣ በቡድን ሰባት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንክን፣ ትላንት ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ “ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃንና ኸመቲ(ጀነራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎን) በስልክ አነጋግሬአለሁ፡፡ ሱዳናውያን ወደ ቤተሰቦቻቸው በሰላም እንዲመለሱና እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ሰብአዊ አቅርቦት መዳረስ እንዲችል፣ ለ24 ሰዓት የሚዘልቅ ተኩስ እንዲያቆሙ አሳስቤያቸዋለኹ፤” ብለዋል፡፡

ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃንና “ኸመቲ” በሚለው ስማቸው ይበልጥ ከሚታወቁት ጀኔራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ኃይሎች ጋራ፣ እኤአ በ2021 የተካሔደውን መፈንቅለ መንግሥት ለማካሔድ አንድ ላይ የተባበሩ ቢኾንም፣ ወደ ኋላ ላይ ግን፣ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተነሣሥተዋል፡፡

ወደ ሲቪል መንግሥት የሚደረገው ሽግግር መገታቱን ተከትሎ፣ ተቃዋሚዎች በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ፣ በካርቱም ጎዳናዎች ሰልፎችን አካሒደዋል፡፡ ዋይት ሐውስ፣ ሰላም ለማምጣት ብርቱ ጥረት እያደረገ መኾኑን ገልጿል፡፡ ይኹን እንጂ፣ ተዋጊዎቹ ወገኖች ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ባይሆኑ፣ ምን ሊከተል እንደሚችል ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒየር፣ “ግጭቱን ማርገብ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ተናግረናል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ይህን አስመልክቶ የተናገሩትን ሰምታችኋል፤ ባልደረቦቼ ያሉትንም እንዲሁ ሰምታችኋል፡፡ እነርሱ ከተናገሩት በላይ የምጨመረው ነገር የለም፤” ብለዋል፡፡ የአፍሪካን ጉዳዮችን በቅርበት የሚያውቁ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት፣ ሁኔታው አደገኛ መኾኑን ይናገራሉ፡፡

ሱዳን ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እያሽቆለቆለች የመሆን ዕድልዋ ርግጥ ሊሆን ስለሚችል፣ ለዚያ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ፣ ይህ የእርስ በርስ ውጊያ በፍጥነት የውክልና ጦርነት ሊሆን የሚችልበት ዕድል መኖሩ ነው፤”

“አሁንም ቢሆን፣ ይህን ግጭት ለማቆም የሚያስችል መንገድ ስላለ ተስፋ አልቆረጥሁም፤” ሲሉ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አባሉ የዴላዌሩ ሴነተር ክሪስ ኩንስ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ኩንስ አያይዘውም፣ “ሱዳን ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እያሽቆለቆለች የመሆን ዕድልዋ ርግጥ ሊሆን ስለሚችል፣ ለዚያ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ፣ ይህ የእርስ በርስ ውጊያ በፍጥነት የውክልና ጦርነት ሊሆን የሚችልበት ዕድል መኖሩ ነው፤” በማለት ያላቸውን ስጋት አክለዋል፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት፣ የዋሽንግተንና የካርቱም ግንኙነት፣ ለረጅም ጊዜ ሻክሮ የቆየ ከመኾኑ ባሻገር፣ ዩናይትድ ስቴትስ እኤአ የ2021ዱን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ ለሱዳን የምትሰጠውን ርዳታ አቋርጣለችና ለውጥ አምጪ የሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ለማሳደር ብዙም የሚያወላዳት አይኾንም፡፡

በስትራቴጂያዊ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ከፍተኛ አባል የሆኑት ካምረን ሃድሰን፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በአደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “እኔ እንደሚመስለኝ፣ አሁን ያለው ፈተና፣ ዋሽንግተን የቀራት አንድ ዐቅም ቢኖር፣ የቅጣት ርምጃ ነው፤ ያን ደግሞ መጠቀም አትፈልግም፤” ያሉት ሃድሰን፣ “እንደሚመስለኝ ባለፉት ስድስት ወራት፣ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ሳይቀር የተመለከታችኹት፣ ዋሽንግተን፥ ተፋላሚ የጦር ጀነራሎቹን ሥልጣን እንዲያጋሩና እንዲለቁ ለማግባባት የተከተለችው ስትራቴጂ፣ የጥቅም ማበረታቻ መስጠት እና አሳታፊነት ነው፤” ብለዋል፡፡ “ችግሩ ግን” ይላሉ ሃድሰን፣ “በሱዳን ታሪክ፣ እነዚህ ጀነራሎች ለማበረታቻዎች ምላሽ የመስጠት ታሪክ የሌላቸው መኾኑ ነው፡፡ አገሪቱን በማስፈራራት፣ በማሸማቀቅ እና በራሳቸው የቅጣት ርምጃዎች እንደሚመሩት ሁሉ፣ ለራሳቸው የሚገባቸውም እርሱ ነው፤” ሲሉ፣ ያለውን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

“አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችለን ዐቅም አለን፤ ይኹን እንጂ ሌሎች በክልሉ ብዙ ፍላጎት እና የራሳቸው ዐቅም ያላቸው አሉ፡፡ ከእነርሱ ጋራ በቅርበት ተባብረን መሥራት ይኖርብናል፤”

ሴነተር ኩንስ፣ “ይህ ሥራ የቡድን ጥረት ነው መኾን ያለበት፤” ሲሉ ይመክራሉ፡፡ “አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችለን ዐቅም አለን፤ ይኹን እንጂ ሌሎች በክልሉ ብዙ ፍላጎት እና የራሳቸው ዐቅም ያላቸው አሉ፡፡ ከእነርሱ ጋራ በቅርበት ተባብረን መሥራት ይኖርብናል፤” ብለዋል ኩንስ፡፡ ርምጃው፥ ከአረብ ሊግ፣ ከግብጽ እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋራ በመሆን ተጀምሯል፡፡ ሁሉም ሰላም ለማምጣት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ጥያቄው ግን፣ ሱዳንን ለአስከፊ ውድመት እና ሰብአዊ ቀውስ የሚዳርጋትን እሳተ ነበልባል፣ ከካርቱም ማውጣት የሚችሉት፣ በምን ያህል ፍጥነት ነው፤ የሚለው ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሱዳን ያለውን ቀውስ የሚከታተል፣ አንድ ልዩ ኃይለ ግብር ማቋቋሙን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል፡፡

XS
SM
MD
LG