በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ተኩስ ማቆሙ ከሸፈ


በካርቱም አወራጎ ዳናዎች ላይ ለአምስተኛ ቀን ለቀጠለው ውጊያ የቃጠሎ አደጋ በከተማዎቹ ተስፋፍቷል
በካርቱም አወራጎ ዳናዎች ላይ ለአምስተኛ ቀን ለቀጠለው ውጊያ የቃጠሎ አደጋ በከተማዎቹ ተስፋፍቷል

በሱዳን ታስቦ የነበረው የ24 ሠዓት ተኩስ ማቆም ከሽፎ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ ልውውጣቸውን ቀጥለዋል፡፡

የመዲናዋ ካርቱም ሰማይ በጭስ ሲጠቁር፣ በሚሊዪን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በዚህ የረመዳን ጾም ወቅት ቤታቸው ለመደበቅ ተገደዋል፡፡

በሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደግሞ ካርቱምን ለቀው እየወጡ እንደሆነ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በካርቱም አወራጎ ዳናዎች ላይ ለአምስተኛ ቀን ለቀጠለው ውጊያ የአገሪቱ ሠራዊት ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተጠያቂ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ኽመቲ መካከል ለወራት የቆየው ውጥረት ባለፈው ቅዳሜ ወደ ጎዳና ላይ የተኩስ ልውውጥ ተቀይሯል፡፡

ሁለቱ ጀነራሎች ከሁለት ዓመታት በፊት በአብደላ ሃምዶክ የሚመራውን የሽግግር መንግሥት በጋራ በመፈንቅለ መንግስሥት አስወግደው የነበረ ሲሆን ወደ ሲቪል መንግሥት የሚደረገውን ሽግግር በተመለከተ እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ወደ መደበኛው ሠራዊት የሚቀላቀልበትን መንገድ በተመለከተ ለወራት ውዝግብ ላይ ከርመዋል፡፡

በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት እስከ ትናንት ድረስ 270 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 2 ሺሕ 600 የሚሆኑት ደግሞ ተጎድተዋል፡፡

የቪኦኤው ማይክል አቲት እንደዘገበው በርካታ ሆስፒታሎች ጉዳት ስለደረሰባቸው ወይም በጸጥታ ሥጋት ምክንያት ተዘግተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG