የአፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ታሊባን ከዚያች ሃገር መውጣት የሚፈልጉ የሀገሪቱ ዜጎች እና የውጭ ሀገር ሰዎች በሙሉ ያለምንም ጉዳት መውጣት የሚችሉበትን መንገድ እንዲያመቻች የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ትናንት ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ያረቀቁትን ውሳኔ ከአስራ አምስቱ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት መካከል ሩስያ እና ቻይና ድምጽ ተአቅቦ ሲያደርጉ የተቀሩት በሙሉ ደግፈውታል።
ታሊባን በአየርም ይሁን በየብስ ከሀገሪቱ ለመውጣት የሚፈልጉ አፍጋኒስታናውያንን አንከለክልም ሲል ባለፈው ሰኞ መግለጫ መስጠቱን ያስታወሰው ምክር ቤቱ ታሊባን ይህን ቃሉን እንዲያከብር እንጠብቃለን ብሏል። ይህን ብቻ ሳይሆ አፍጋኖች እና የውጭ ሃገር ዜጎች ደህንነታቸው በሚጠበቅበት እና ስርዓት ባለው መንገድ እንዲወጡ የገባውን ቃል ሁሉ ማክበር ይኖርበታል ሲል የጸጥታው ምክር ቤት አስገንዝቧል።
ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረበት ዕለት ጀምሮ በዓለም አቀፉ አውሮፕላን ጣቢያ ያለውን ትርምስ የሚያሳዩት ምስሎች በርካታ አፍጋኖች ለመውጣት ምን ያህል እየተጣደፉ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ 122,000 አሜሪካውያን፣ የአፍጋኒስታን እና የሌሎችም ሀገሮች ዜጎች እንዲወጡ ማድረጓን ገልጸዋል። ታሊባን ዛሬም ነገም ሆነ ከነሃሴ 31 በኋላም ይሁን መውጣት የሚፈልጉ አፍጋኖች እና ሌሎችም ዜጎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ የሚወጡበትን መንገድ ለማቻቸት የገባውን ቃል እንዲያከብር በጸጥታ ምክር ቤቱ ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።
ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከኔቶ ሃይሎች ጋር በአስተርጓሚነት እና በሌሎችም ዘርፎች አብረው የሰሩ የሀገሪቱ ተወላጆች ታሊባኖች የበቀል ጥቃት ያደርሱብናል ብለው ፈርተዋል።
የሀገሪቱ ሴቶች እና ውህዳን የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ታሊባን በ1990ዎቹ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ወደነበረው አፈና እና የሰብዐዊ መብት ረገጣ መመለሳችን ነው ብለው ሰግተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የተመድ አምባሳደር ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፣
"የሀገሪቱን ህዝብ በሙሉ ባውሮፕላን ልናስወጣ አንችልም። አሁን ወቅቱ ዲፕሎማሲውን ማጠናከር የሚገባበት ነው ሲሉ" አመልክተዋል።
የጸጥታ ምክር ቤቱ ባለፈው ሃሙስ በርካታ አፍጋኖች እና አስራ ሦስት አሜርካውያን ወታደሮች የገደለውን ፍንዳታ እጅግ የሚወገዝ ጥቃት ሲል አጥብቆ ኮንኖታል።
ጥቃቱን ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን ቅርንጫፍ የሆነው አይሲስ ኮራሳን የተባለው ቡድን ለጥቃቱ ሃላፊነት መውስዱ ይታወቃል።